ሐምሌ 07/2013 (ዋልታ) – የአፍሪካ ህብረት የቀድሞውን ፕሬዝዳንት የጃኮብ ዙማ መታሰርን በመቃወም በደቡብ አፍሪካ የተከሰተውን ሁከት በጥብቅ አውግዟል።
የቀድሞው ፕሬዝዳንት ጃኮብ ዙማ ፈጽመዋል በተባለው ከፍተኛ የሙስና ወንጀል የሀገሪቱ ፍርድ ቤት እንዲታሰሩ የወሰነውን ውሳኔ በመቃወም በተነሳው ሁከት እና ብጥብጥ እስካሁን የ72 ሰዎች ሰዎች ህይወት አልፏል ተብሏል።
የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ መሃማት በሀገሪቱ እየተካሄደ ያለውን የንጹሃን ዜጎች ግድያ እና የንብረት ዝርፊያ አውግዘዋል።
በሀገሪቱ የተለያዩ ከተሞች በተቀሰቀሱ የተቃውሞ ሰልፎች ዝርፊያና የንብረት ውድመት ደርሷል።
ኮሚሽኑ በመግለጫው በደቡብ አፍሪካ የዜጎች ሞት፣ የህዝብ እንዲሁም የግለሰቦች ንብረት የዘረፉ ትዕይንቶችን በከፍተኛ ሁኔታ በማውገዝ ሁከቱ እንዲቆም ጠይቋል፡፡
መንግስት በበኩሉ ሁከቱን ለመቋቋም ሰራዊት ያሰማራ ሲሆን፣ በዚህም በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በቁጥጥር ስር ውለዋል ተብሏል፡፡
ህብረቱ በደቡብ አፍሪካ የህግ የበላይነት እንዲከበር፣ ሰላምና መረጋጋት በፍጥነት ወደነበረበት እንዲመለስ ጥሪ አቅርቧል፡፡
የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን የተፈጠረውን ሁከት እና ብጥብጥ መፍታት አለመቻል በሀገርና በአህጉር ላይ “ከባድ ተጽዕኖዎች” እንደሚኖሩት መግለጹን ኢዜአ ዘግቧል።