ግንቦት 02/2013 (ዋልታ) – የአፍሪካ ልማት ባንክ እና የገንዘብ ሚኒስቴር የ1 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር ድጋፍ ስምምነት ተፈራረሙ፡፡
የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ያስሚን ዎሃብረቢ እና የአፍሪካ ልማት ባንክ የምስራቅ አፍሪካ ቀጠና ምክትል ዳይሬክተር ዶክተር አብዱል ካማራ ስምምነቱን ተፈራርመዋል።
የአፍሪካ ልማት ባንክ ለኢትዮጵያ ያደረገው 1 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር /የ31 ሚሊዮን ዶላር / ድጋፍ የህጻናት መቀንጨርን ለመከላከል ለሚደረገው ጥረት አጋዥ መሆኑን ሚኒስትር ዴኤታዋ ገልጸዋል።
የተደረገው ድጋፍ ኢትዮጵያ የህጻናትን ስር የሰደደ የተመጣጠነ ምግብ እጥረትንና የመጨንቀር ችግር ለመፍታት የምታደርገውን ጥረት እንደሚያግዝ ተገልጿል፡፡
የፋይናንስ እገዛው በሰቆጣ ቃልኪዳን መመሪያ ፕሮግም መሰረት በአማራና በትግራይ በሚገኙና የመቀንጨር ችግሩ ጎልቶ በሚታይባቸው የተመረጡ የክልሎቹ ወረዳዎች ይውላል ተብሏል፡፡
በዚህም ከተመጣጠነ ምግብ ጋር በተያያዘ በአካባቢዎቹ የሚከናወኑ ተግባራትንና ለስኬቱ አጋዥ የሆኑ የመሰረተ ልማት አቅርቦት ፍላጎትን ለማሟላት ይረዳል ተብሏል፡፡
በተጨማሪም ኢትዮጵያ የህፃናትን የተመጣጠነ የምግብ እጥረት በዘለቄታው ለመፍታት ያጸደቀችውን የሰቆጣ ቃል ኪዳን እውን ለማድረግ እንደሚያግዝም ሚኒስቴር ዴኤታዋ ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ በሰቆጣ ቃል ኪዳን በመታገዝ የህጻናትንና የነፍሰጡር እናቶችን አመጋገብ በማሻሻል በርካታ ስኬቶችን ማስመዝገቧን በመጥቀስ ድጋፉ የበለጠ ስራ ለማከናወን አጋዥ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ድጋፉ በእናቶችና ህጻናት አመጋገብ ዙሪያ እውቀት እና አመለካከትን ለማሻሻል የሚያስችሉ ስራዎች የሚከናወኑበት መሆኑንም ተናግረዋል።
የተመጣጠነ ምግብ እጥረት የአንድ አገርን የልማት ጉዞ በእጅጉ እንደሚያደናቅፍ በመግለጽ ድጋፉ ኢትዮጵያ የምግብና የተመጣጠነ አመጋገብ ስትራቴጂን ተግባራዊ ለማድረግ የያዘችውን ጥረት ያግዛል ብለዋል፡፡
የአፍሪካ ልማት ባንክ ኢትዮጵያ የሚያከናውናቸውን የተለያዩ የልማት ስራዎች ለማገዝ ለሚያደርገው ድጋፍም ምስጋና አቅርበዋል።
የአፍሪካ ልማት ባንክ የምስራቅ አፍሪካ ቀጠና ምክትል ዳይሬክተር ዶክተር አብዱል ካማራ፤ የኢትዮጵያ መንግስት የህፃናት የመቀንጨር ችግርን ለመከላከል የሚያደርገውን ጥረት አድንቀው ለዚህም ድጋፍ መደረጉን ጠቅሰዋል።
ኢትዮጵያ ባለፉት 10 ዓመታት የህጻናትና እናቶች ስርአተ ምግብ ለማሻሻልና የህፃናት የመቀንጨር ችግርን ለመከላከል እየሰራች መሆኑንም ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ የህጻናት የመቀንጨር ችግርን እኤአ እስከ 2030 ለማጥፋት አቅዳ እየሰራች መሆኑ ይታወቃል።
የአፍሪካ ልማት ባንክ በአፍሪካ የተለያዩ የልማት ስራዎችን እያገዘ መሆኑን ገልጸው፤ ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።