የአፍሪካ ቀን መከበር የአፍሪካውያንን አብሮነት ለማጎልበት ይጠቅማል ተባለ

ግንቦት 26/2014 (ዋልታ) የአፍሪካ ቀን መከበር አፍሪካውያን የጋራ እሴቶቻቸውን በማጠናከር አብሮነታቸውን ለማጎልበት እንደሚጠቅም በኳታር የኢፌዲሪ ልዩ መልዕክተኛና ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ፈይሰል አሊይ ገለጹ።
የአፍሪካ ቀን በዓል በኳታር ዶሃ የዲፕሎማቲክ ክለብ ከ30 በላይ የአፍሪካ አገራት ሚሲዮን መሪዎች እና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው ዓለም ዐቀፍ ተቋማት ተወካዮች በተገኙበት ተከብሯል።
በበዓሉ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት አምባሳደር ፈይሰል የአፍሪካ ቀን መከበር ዘርፈ ብዙ ፋይዳ እንዳለው ገልጸዋል።
“የአፍሪካ ቀን በዓል መከበር አፍሪካውያን ነጻነታቸውንና የጋራ ጥቅሞቻቸውን ለማስጠበቅ በእጅጉ ይጠቅማል” ብለዋል።
አፍሪካውያን የጋራ እሴቶቻቸውን በማጠናከር አብሮነታቸውን ለማጎልበት እንደሚጠቀሙበትም አመልክተዋል።
በዓሉን በንግግር የከፈቱት በኳታር የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳዮች ዳይሬክተር አምባሳደር አብደላህ ቢን ሃሰን አል ጃብር በበኩላቸው ኳታር ከአፍሪካ ጋር ረጅም ጊዜ ያስቆጠረ ጥብቅ ወዳጅነት እንዳላት አስታውሰዋል።
“ኳታር ግንኙነቱን አጠናክሮ ሁለንተናዊ ትስስሩን የማስቀጠል ልዩ ፍላጎት አላት” ብለዋል።
የአፍሪካ 2063 የልማት ግብን ለማሳካት ይቻል ዘንድ የአፍሪካ አገራት ከተቀረው የዓለም ክፍል ጋር የሚኖራቸውን ሁለንተናዊ ትስስር ማጠናከር አስፍላጊ እንደሆነ በመድረኩ ተገልጿል።
በዚህ ሂደት ኳታር በአፍሪካ የምትጫወተው አዎንትዊ ሚና ተጠናክሮ የሚቀጥል ለመሆኑ በርካታ ማሳያዎች አሉ ተብሏል።
በዝግጅቱ ላይ ተቀመጭነታቸውን በኳታር ዶሃ ያደረጉ የአፍሪካ አገራት ኤምባሲዎችና ዜጎቻቸው የተሳተፉ ሲሆን የኢትዮጵያ ኤምባሲም በኳታር የኢትዮጵያ ኮሚዩኒቲ ማኅበር ጋር በመቀናጀት የኢትዮጵያን የባህል አልባሳትን ቁሳቁሶችን አቅርቧል፡፡
በተጨማሪም ባህላዊ ምግቦችን የማቅመስ እንዲሁም የኢትዮጵያ ቡና አፈላል ሥነ-ሥርዓትም አካሂዷል ሲል የዘገበው ኢዜአ ነው።