የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ከሱዳኑ ጄኔራል መሀመድ ዳጋሎ ጋር ተወያዩ

                  የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር

ጥር 15/2014 (ዋልታ) የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ማህመት ከሱዳን ሉኣላዊ የሽግግር ምክር ቤት ምክትል ፕሬዝዳንት ጄኔራል መሀመድ ሀምዳን ዳጋሎ (ሄመቲ) ጋር ተወያዩ።

የኅብረቱ ኮሚሽን ሊቀመንበር ከሉኣላዊ የሽግግር ምክር ቤቱ ምክትል ፕሬዝዳንት ጋር ‹‹በሱዳን አስጨናቂ ሁኔታዎች ዙሪያ በአዲስ አበባ ተወያይተናል›› ሲሉ በቲውተር ገጻቸው ጽፈዋል፡፡

ምክትል ፕሬዝዳንቱ ትናንት አዲስ አበባ ሲገቡ የመከላከያ ሚኒስትሩ አብርሀም በላይ (ዶ/ር) እና የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተሩ ተመስገን ጥሩነህ አቀባበል እንዳደረጉላቸው ይታወሳል፡፡

ሱዳን በሉኣላዊ የሽግግር ምክር ቤቱ ሊቀ መንበር (ፕሬዝዳንት) ጄኔራል አብዱልፋታህ አልቡርሃን የሚመራው ወታደራዊ ክንፍ መፈንቅለ መንግሥት በማድረግ የሲቪል አስተዳደሩን ማስወገዱን ተከትሎ አገሪቱ ወደ ቀውስ ገብታለች፡፡

ለ3 ዓመት ቆይታ እንዲኖረው ታስቦ የነበረው የሽግግር መንግሥቱ ሲመሰረት የመጀመሪያውን ምዕራፍ ወታደራዊ ክንፉ በበላይነት እንዲመራና ባሳለፍነው ኅዳር 2014 ለሲቪል አስተዳደሩ ለቆ አገሪቱ ለምርጫ እንድትዘጋጅ ማድረግ የሚል ስምምነት ነበረው፡፡

ሆኖም በጄኔራል አልቡርሃን የሚመራው ወታደራዊ ክንፉ ሥልጣን በማስረከቢያው ዋዜማ መፈንቅለ መንግሥት በመፈፀም አገሪቱን ወደ አለመረጋጋት፤ ሕዝቡንም ወደ ከፍተኛ ተቃውሞ አስገብቶት ይገኛል፡፡ በዚህም ሱዳናዊያን የወታደሩን ድርጊት በመቃወም ዛሬም በአደባባይ የሲቪል አስተዳደር ምስረታን እየጠየቁ ይገኛሉ፡፡

ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://www.facebook.com/waltainfo
ቴሌግራም https://t.me/WALTATVEth
ዩቲዩብ https://www.youtube.com/c/WaltaTV/featured
ቲዊተር https://twitter.com/walta_info
አብራችሁን ስላላችሁ እናመሰግናለን!