ሰኔ 3/2014 (ዋልታ) የወቅቱ የአፍሪካ ኅብረት ሊቀመንበር የሆኑት የሴኔጋል ፕሬዝዳንት ማኪ ሳል ዩክሬን የእህልን ወጪ ንግድ ለማቃለል ከኦዴሳ ወደብ ፈንጂዎችን እንድታስወግድ ጠየቁ።
ሊቀ መንበሩ ይህንን ያሉት ከፈረንሳይ ሚዲያዎች አርኤፍአይና ፍራንስ 24 ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ሲሆን ሩሲያ በኦዴሳ ላይ ጥቃት እንደማትፈፅም ከፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ማረጋገጫ እንደደረሳቸውም ተናግረዋል።
ሩሲያ የዩክሬን የስንዴ ወጪ ንግድ እያደናቀፈች ነው የተባለ ሲሆን ሩሲያ ግን አስተባብላለች። ሩሲያ እንደምትለው ዩክሬን መተላለፊያ የሆነው ኦዴሳ እና ሌሎች ወደቦች ዙሪያ ያለውን አካባቢ ፈንጆች ማንሳት አለባት።
የዩክሬን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በበኩሉ ዩክሬን በወደቦቿ ዙሪያ ያሉትን ፈንጆች ማንሳት አትችልም ብለዋል። ለዚህም ምክንያታቸው ሩሲያ “ደቡባዊ ዩክሬንን ለማጥቃት የእህል መተላለፊያ ኮሪደሮችን ትጠቀማለች” የሚል ነው ተብሏል።
የእህል ወጪ ንግድ ወደ አፍሪካ እንደገና ካልተጀመረ በዩክሬን እና በሩሲያ የእህል ምርቶች እና ማዳበሪያዎች ላይ ጥገኛ ለሆነችው አኅጉር አሳሳቢ የሆነ የረሃብ ሁኔታ ውስጥ እንደሚከታትና ከፍተኛ ጉዳትም እንደሚያስከትል አስረድተዋል።
ሩሲያ እና ዩክሬን 29 በመቶ የሆነውን የዓለም ዐቀፍ የስንዴ ወጪ ንግድን ይሸፍናሉ።
ሊቀ መንበሩ በአሁኑ ወቅት ፈረንሳይ ውስጥ የሚገኙ ሲሆን በዛሬው ዕለትም ከፈረንሳዩ አቻቸው ኢማኑኤል ማክሮን ጋር ይወያያሉ ተብሎ ይጠበቃል።
በዋነኝነትም ሩሲያ በዩክሬን ላይ በፈጸመችው ወረራ ምክንያት የአውሮፓ ኅብረት የጣለውን ማዕቀብ እንዲነሳ ፕሬዝዳንት ማክሮን ግፊት እንዲያደርጉ ይጠይቃሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ቢቢሲ ዘግቧል።