የአፍሪካ ኅብረት ጉባኤ ኢትዮጵያዊያን የሀገራቸውን ሰላምና መረጋጋት ለዓለም በግልፅ የሚያሳዩበት ነው ተባለ

ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር)

ጥር 19/2014 (ዋልታ) በቀጣይ ሳምንት የሚካሄደው የአፍሪካ ኅብረት ጉባኤ ኢትዮጵያ የራሷን ችግሮች በራሷ ልጆች በመፍታት አንድነቷን ጠብቃ የቀጠለች ሀገር መሆኗን የምታሳይበት እንደሚሆን የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ገለፀ፡፡

የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) ዛሬ በሰጡት መግለጫ ጉባኤው ኢትዮጵያዊያን የሀገራቸውን ሰላም እና መረጋጋት ለዓለም በግልፅ የሚያሳዩበት እንደሚሆን ገልጸዋል፡፡

የሀገሪቱን ወቅታዊ ሁኔታ ከግምት ውስጥ በማስገባት በኢትዮጵያ የቱሪዝም ፍሰት እንዳይኖር፣ ልዩ ልዩ ዓለም ዐቀፍ ኮንፈረንሶች ስብሰባዎች እንዳይካሄዱ ከፍተኛ ቅስቀሳ እየተደረገ እንደሚገኝ ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡

የጉባኤው ተሳታፊዎች በአንዳንድ የዓለም ዐቀፉ ማኅበረሰብ አባላት የሚደረጉባቸውን ጫናዎች ወደ ጎን ትተው ለኅብረቱ ሕግና መርሆዎች ተገዢ በመሆን ጉባኤው የኅብረቱ መቀመጫ በሆነችው በአዲስ አበባ መደበኛ ባህሪውን ጠብቆ እንዲካሄድ መወሰናቸው በእጅጉ የሚያስመሰግናቸው እንደሆነም ገልፀዋል፡፡

በኅብረቱ ጉባኤ የሚሳተፉ ሰዎች በሚንቀሳቀሱባቸው ቦታዎችም ይሁን በቱሪዝም መስህቦች ጥሩ ጊዜ በማሳለፍ በጎ ትዝታን ይዘው እንዲሄዱ ሁሉም ኢትዮጵያዊ የበኩሉን ኃላፊነት እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል፡፡