የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጠና ለኢንዱስትሪ ፓርኮች ሰፊ የገበያ ዕድል እንደሚፈጥር ተገለጸ

መጋቢት 18/2013(ዋልታ) አዲሱ የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጠና ስምምነት ለኢንዱስትሪ ፓርኮች አስተማማኝና ሰፊ የገበያ ዕድል እንደሚፈጥርላቸው የንግድ ሚኒስቴር አስታወቀ።

በንግድ ሚኒስቴር የንግድ ግንኙነትና ድርድር ዳይሬክተር አቶ ሙሴ ምንዳዬ በተለይ ለኢትዮጵያ ፕሬስ እንደገለጹት፤ የአፍሪካ ነፃ ገበያ ስምምነቱ በዋናነት የኢንዱስትሪ ፓርኮች ጥሬ ዕቃን ከአፍሪካ አገራት በማስገባት በሙሉ አቅማቸው አምርተው በስፋት ወደ ገበያ እንዲገቡ ያስችላቸዋል።

ስምምነቱን ታሳቢ አድርገው ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡ ጥሬ እቃዎች በሀገር ውስጥ የማይመረቱ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ሙሴ፤ ስምምነቱ ከዚህም በላይ የአፍሪካውያንን ግንኙነት በማጠናከር የገበያ ተወዳዳሪነታቸውን ከፍ እንደሚያደርገው አስታውቀዋል።

ነፃ ገበያው በአሜሪካና በአውሮፓ ፍቃድ ላይ የተንጠለጠለውን የሀገራቱን የወጭ ንግድ ከስጋት በማውጣት በዘላቂነት በአፍሪካ ገበያዎች እንዲገቡ ያደርጋልም ያሉት አቶ ሙሴ፣ ኢንዱስትሪያል ፓርኮች በሙሉ አቅማቸው እንዲያመርቱ በማድረግ የገበያ ዕድሎችን እንደሚፈጥር አመልክተዋል።