ሚያዝያ 7/2013(ዋልታ) – የአፍሪካ አገራት በድርጅቱ ፀጥታ ምክር ቤት ተወካይ እንዲኖራቸው የሚነሳው ጥያቄ መታየት እንደሚገባው በኢትዮጵያ የሩሲያ አምባሳደር ያቭጋኒ ተርካን ገለፁ። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ራሱን ሪፎርም ማድረግ እንደሚኖርበትም ጠቁመዋል።
አምባሳደሩ “ድርጅቱ ሲቋቋም ዓለም አንድ ገጽታ ነበራት። አሁን የዓለም ሁኔታዎች ተቀይረዋል፤ ድርጅቱ ደግሞ እንደማንም ሕያው አካል መኖር አለበት፤ ለዚህም መለወጥ አለበት” ብለዋል።
ድርጅቱ ከተመሰረተ ረጅም ዕድሜ በማስቆጠሩ እና የዓለም ገጽታዎች በመቀያየራቸው ጊዜውን የሚመጥን እና ለሁሉም አገራት እኩል ሃላፊነት የሚወስድ አደረጃጀት እንዲኖረው ሩሲያ ፍላጎት እንዳላትም ገልፀዋል።
ሂደቱን በከፍተኛ ጥንቃቄ ማየት ይገባል ያሉት አምባሰደሩ፤ ይህ ድርጅት በተቋቋመበት ወቅት ለዓለም ሕዝቦች ያገለግል ዘንድ ከፍተኛ ጥረት ተደርጎ እንደነበር አስታውሰዋል። በእውነቱ በዚህ ድርጅት አሠራሮች ምናልባትም አንዳንድ ነገሮች የማንወድ ልንሆን እንችላለን። አንዳንድ ጊዜ ቢሮክራሲ ይበልጣል። ያም ሆነ ይህ ብቸኛ የሆነ ትልቁ የዓለም ድርጅት ነው፤ ይህንን ድርጅት ለማሻሻል ጥረት በምናደርግበት ወቅት ነገሮችን እንዳናበላሽ መጠንቀቅ አለብን ብለዋል።
በሌላ በኩል በመንግሥታቱ ድርጅት በኩልም ቢሆን ተመሳሳይ ነገር እንደሚያስፈልግ አምባሳደሩ ተናግረዋል።
በዚህ ሂደት ደግሞ ሁለቱም አገሮች ሩሲያ እና ኢትዮጵያ የድርጅቱ መሥራች አገሮች መካከል በመሆናቸው የተለየ ኃላፊነት በድርጅቱ ውስጥ አላቸው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።