የአ/አ አስተዳደር ለወሎና ቦረና ድጋፍ አደረገ

ጥቅምት 17/2014 (ዋልታ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በአማራ ክልል ወሎ እና ቦረና እገዛ ለሚፈልጉ ወገኖች ድጋፍ አደረገ፡፡
በአሸባሪው ሕወሓት ወረራና ጥቃት በወሎ አካባቢ ለተፈናቀሉና በከፋ ችግር ውስጥ ለሚገኙ ወገኖች በ2ኛ ዙር ድጋፍ ከ7 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የምግብ፣ ምግብ ነክ፣ አልባሳት እና የንፅህና መጠበቅያዎችን ድጋፍ አድርጓል፡፡
አስተዳደሩ ከዚህ ቀደም በአማራ ክልል ግንባር ለሚገኘው የፀጥታ ኃይልና ለተፈናቀሉ ወገኖች የሚሆን 385 ሚልዮን ብር በላይ የገንዘብ ድጋፍ ማድረጉ የሚታወስ ነው፡፡
በተያያዘ ዜና የከተማ አስተዳደሩ የዝናብ እጥረት ባስከተለው ድርቅ የእንስሳት ሃብታቸውን እያጡ ለሚገኙ የቦረና ዞን ነዋሪች 16 የውሀ ቦቴ፣ 13 የእንስሳት መኖ የጫኑ ተሽከርካሪዎችን ወደ ስፍራው ልኳል።
የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ለወገኖቻችን አለኝታነታችንን ለማረጋገጥ የሚያስችል ድጋፍ ማድረጋችንን እንቀጥላለን ብለዋል፡፡
ምንም እንኳን ኢትዮጵያ ፈተናዎች እየገጠሟት ቢሆንም በተባበረ ክንድ እየታለፈ እንደሚገኝም ከንቲባ አዳነች ተናግረዋል።
በሚልኪያስ አዱኛ