የኢትዮጵያና ህንድ ግኑኝነት ዘመን ተሻጋሪ ነው – የህንድ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር

ሰኔ 15/2014 (ዋልታ) የኢትዮጵያና ህንድ ግኑኝነት በብዙ ነገር የተሳሰረ ዘመን ተሻጋሪ ነው ሲሉ የህንድ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሱብራማኒያም ጃይሸንከር ተናገሩ።

ሚኒስትሩ ከኢፌዴሪ ሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) እና ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ተስፋዬ ይልማ ጋር በመሆን በአዲስ አበባ የሚገኘውን የህንድ ኤምባሲ ህንፃ መርቀዋል።

በምረቃው ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የሁለቱን ሀገራት ወዳጅነት በሚመለከት ገላፃ ያደረጉት ሚኒስትሩ ህንድ ከኢትዮጵያ ጋር በንግድና ኢንቨስትመን በባህል በትምህርትና በሌሎች መስኮች በትብብር እየሰራች መሆኑን ተናግረዋል።

ህንድ በአሁን ሰዓት ከአፍሪካ ሀገራት ያላትን ግኑኝነት ለማጠናከር በተለየ ትኩረት እየሰራች መሆኑን ያስታወሱት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ከኢትዮያ ጋር ያለንን ዘርፈ ብዙ ወዳጅነት የላቀ ለማድረገ የጋራ ጥቅምን መሰረት በማድረግ በትብብር እንሰራለን ሲሉ ተናግረዋል።

የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትሯ ኤርጎጌ ተስፋዬ ዛሬ የተመረቀው የኤምባሲ ህንፃ የኢትዮጵያ መንግሥት የሁለቱን ወዳጃሞች ሀገራት የነበረ ግኑኝነትን በይበልጥ ለማጠናከር ያለውን ፅኑ ፍላጎት የሚያሳይ ነው ብለዋል።

በአሁን ሰዓት 637 የህንድ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ በተለያዩ የኢንቨስትመን መስኮች ተሰማርተው እንዳሉ ያስታወሱት ሚኒስትሯ በሀገራቱ መካከል ያለው የንግድ ልውውጥም ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱን መናገራቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኝነው መረጃ ነው ያመላከተው።