የኢትዮጵያና ሩሲያ ፌደሬሽን ምክር ቤቶች በጋራ ለመስራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረሙ

ግንቦት 9/2015 (ዋልታ) የኢትዮጵያ እና ሩሲያ ፌደሬሽን ምክር ቤቶች በጋራ ለመስራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረሙ፡፡

በፌደሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር የተመራ የልዑካን ቡድን በሩሲያ ፌዴሬሽን የሥራ ጉብኝት እያካሄደ ይገኛል።

አፈ ጉባኤው ሩሲያ ፌዴሬሽን የፌዴራላዊ ሸንጎ አፈጉባኤ ቫለንቲና ማቲቭኔኮ ጋር የሁለቱን አገራት የሁለትዮሽ ግንኙነትና የባለብዙ ወገን ትብብር ማጠናከር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ተወያይተዋል፡፡

ምክር ቤቶቹ በጋራ ለመስራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ስምምነት ያደረጉ ሲሆን ስምምነቱ ኢትዮጵያና ሩሲያ በፖለቲካውና በኢኮኖሚው ዘርፍ ያላቸውን ግንኙነት እንዲያጎለብቱ የሚያስችል መሆኑ ተገልጿል።

በሁለቱ ፌዴሬሽኖች የተደረሰው ስምምነት በአቅም ግንባታ እና ልምድ ልውውጥ ላይ የሚያተኩር ሲሆን ኢትዮጵያ ብዘኃነትን በአግባቡ በማስተናገድ፣ በህገ መንግስት ትርጉም፣ በመንግስታት ግንኙነት፣ በሀብት እና በጀት ክፍፍል እንዲሁም ጠንካራ የፌደራል ስርአት በመገንባት አኳያ ከሩሲያ ጠቃሚ ልምድ እንደምትቀስም ተነስቷል።

አፈ ጉባኤ አገኘው ከሩሲያ የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ ግሩዝዴቭ አሌክሴይ ጋር ባደረጉት ውይይት ኢትዮጵያና ሩሲያ በፖለቲካና በዲፕሎማሲ መስክ ያላቸውን ጠንካራ ግንኙነት ወደ ኢኮኖሚው ዘርፍ በተለይም ወደ ንግድና ኢንዱስትሪ ትስስር ዘርፍ ማጎልበት እንደሚያስፈልግ መግባባት ላይ መድረሳቸው ተጠቁሟል።

የኢትዮጵያን የወጪ ምርቶች በቀጥታ ወደ ሩሲያ ለማስገባት ያሉ ዕድሎችን ለማጥናትና፣ የወጪና የገቢ ምርቶችን አይነት ለማበራከት እና በኢንዱስትሪ ዘርፍ በጋራ ለመንቀሳቀስ ከመግባባት ላይ መደረሱም ተገልጿል፡፡

የልዑካን ቡድኑ ከሌሎች የሩሲያ የመንግስት ተቋማት ጋር የሁለቱን አገራት ግንኙነት ማጠናከር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ መወያየቱም ተገልጿል፡፡

አፈ ጉባኤው በሩሲያ ከሚገኙ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አባላት ጋር በአገራዊ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ መወያየታቸውም ተመልክቷል።

ከሩሲያው የማዕድን ሀብቶች ኤጀንሲና የሩሲያና ኢትዮጵያ የኢኮኖሚ፣ የሳይንስና እና የቴክኒክ ትብብር የጋራ ኮሚሽን የሩሲያ ወገን ሊቀመንበር ከሆኑት ሚስተር ፔትሮቭ ጋር በተደረገው ውይይትም ሩሲያ ከፍተኛ ልምድ ካካበተችበት የማዕድን ዘርፍ ልምድ ማካፈል በሚቻልባቸው መንገዶች ላይ ተወያይተዋል።

የሩሲያ ባለሀብቶች በኢትዮጵያ ኢንቨስት በሚደርጉበትና ሩሲያ እያደረገች ያለውን የፋይናንስና የቴክኒክ ድጋፍ ተጠናክሮ በሚቀጥልበት ሁኔታ ላይ መወያየታቸው ተጠቅሷል፡፡

ሩሲያ ከኢትዮጵያ ጋር በኢኮኖሚው ዘርፍ ያላትን ትብብር ለማጠናከር የሚያስችላትን ፍኖት ካርታ እያዘጋጀች መሆኑም እንዲሁ።

የልዑካን ቡድኑ በሩሲያ ፌዴሬሽን በቀጣይ በሚኖረው ቆይታ ከሩሲያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና ከሌሎች ተቋማት ጋር የሚወያይባቸው መድረኮች እንደሚካሄዱም ከፌደሬሽን ምክር ቤት ማህበራዊ የትስስር ገጽ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።