የኢትዮጵያና የሩስያ የጋራ ኮሚሽን መሪዎች በኢኮኖሚ፣ በሳይንስ፣ በቴክኒክና የንግድ ጉዳዮች ላይ በቪዲዮ ኮንፈረንስ ውይይት ማድረጋቸውን ትምህርት ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
የትምህርት ሚኒስትር ኢንጂነር ጌታሁን መኩሪያ (ዶ/ር) እና በሩስያ ፌደሬሽን የተፈጥሮ ሃብትና የአካባቢ ጉዳዮች ምክትል ሚኒስትርና የፌደራል የማዕድን ሃብት ኤጀንሲ ሃላፊ ኤቫግኒ ኪሰልቭ በቪዲዮ ኮንፈረንስ ተወያይተዋል።
ሁለቱ ሚኒስትሮች ጥቅምት 2019 ላይ የሁለቱ ሀገራት መሪዎች በሩስያ ሴንት ፒተርስበርግ የተስማሙባቸው ጉዳዮች ያሉበትን ደረጃ ገምግመዋል።
የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ኮሚሽኑ የጎላ አስተዋፅኦ ማድረጉ በውይይቱ ተገልጿል።
ኢትዮጵያ የኒውክሌር ቴክኖሎጂን ለሰላማዊ ጥቅም ለማዋል የሚያስችላትን የሁለቱን ሀገራት ስምምነት የኢትዮጵያ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማፅደቁን የጋራ ኮሚሽኑ አድንቋል።
በውይይቱ የኮሚሽኑ 8ኛውን የጋራ ስብስባ 2021 ላይ በአዲስ አበባ ለማድረግ መስማማታቸውን ከትምህርት ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡