የኢትዮጵያና ኳታር ግንኙነት ሰፊ የኢንቨስትመንት እድሎችን የያዘ መሆኑ ተገለጸ

መስከረም 9/2015 (ዋልታ) የጋራ ተጠቃሚነትን መሠረት ያደረገው የኢትዮጵያና ኳታር ግንኙነት ሰፊ የኢንቨስትመንት እድሎችን የያዘ ነው ሲሉ በኳታር የኢትዮጵያ አምባሳደር ፈይሰል አልይ ገለጹ።

አምባሳደሩ ከኳታሩ ፔንንሱላ ጋዜጣ ጋር በነበራቸው ቆይታ ኳታርና ኢትዮጵያ ያላቸው ግንኙነት የጋራ ተጠቃሚነትንና ሉዓላዊነትን ባከበረ መልኩ የተሳሰረ መሆኑን አብራርተዋል።

በባለ ብዙ መስኮች የተሳሰረው ግንኙነቱ በተለይም በኢትዮጵያ ሰፊ የኢንቨስትመንት እድሎችን ያቀፈ ነው ሲሉ አመልክተዋል።

በኢትዮጵያ ያለው ሰፊ የኢንቨስትመንት እድልና መስህቦች ለኳታር ባለ ሃብቶችና ቱሪስቶች ልዩ መዳረሻ ይሆኗቸዋል ማለታቸውን ኢዜአ አስነብቧል፡፡

የሀገራቱ ትስስር ማሳያ ከሆኑት መካከል በኳታር የልማት ፈንድ አማካኝነት በአዲስ አበባ የሚገነባውን ልዩ የኩላሊት ህክምና ሆስፒታልን በማሳያነት ያነሱት አምባሳደር ፈይሰል የሁለቱ ሀገራት መሪዎች የተፈራረሟቸው 13 ስምምነቶች መኖራቸውንና የተወሰኑት ወደ ትግበራ እንደገቡ ገልጸዋል።

ሀገራቱ ያላቸውን ታሪካዊ የሁለትዮሽ ግንኙነት የሚያጠናክር የጋራ የሚኒስትሮች ኮሚሽን በማቋቋም ወደ ስራ መግባታቸውንና በኳታር ከ30 ሺሕ በላይ ኢትዮጵያውያን ለስራ መሰማራታቸውን አንስተዋል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ፒኤችዲ) ተመርቆ የተከፈተው የድሬዳዋ ነጻ ንግድ ቀጠና ኢትዮጵያ የውጭ ኢንቨስትመንት ለመሳብ እያደረገች ካለችው ከፍተኛ እንቅስቃሴ መካከል ዋነኛው መሆኑንም በማብራራት የኳታር ባለሃብቶች እድሉን በመጠቀም በቴክኖሎጂ፣ በማኑፋክቸሪንግ፣ በግብርናና ቱሪዝም ዘርፎች እንዲሰማሩ ጠይቀዋል።

በሀገር ውስጥ የሚገኙ የኢንቨስተመንት መስኮችን ለውጭ ባለሃብቶች ተሳትፎ ክፍት ከማድረግ አካያ መንግስት ከፍተኛ እርምጃዎች መውሰዱንና በቅርቡም በፋይናንስ ሴክተሩ የውጭ ተቋማት እንዲሳተፉ የሚያስችል ረቂቅ መቅረጹን ጠቁመዋል።

በኳታርና በኢትዮጵያ መካከል ያለውን የህዝብ ለህዝብና መንግስት ለመንግስት ግንኙነት በተጠናከረ ሁኔታ ለማሳኬድ እንደሚሰሩም አምባሳደሩ ተናግረዋል።