የኢትዮጵያና የአዘርባጃን አጋርነት ሉኣላዊነትና የግዛት አንድነት መከበርን መሰረት ያደረገ ነው

ኅዳር 17/2014 (ዋልታ) የኢትዮጵያ እና የአዘርባጃን አጋርነት ሉኣላዊነትና የግዛት አንድነትን ባከበረ መልኩ መሆኑን በኢትዮጵያ የአገሪቱ ተጠባበቂ አምባሳደር ሩስላን ናሲቦቭ ገለጹ።

አምባሳደር ሩስላን ናሲቦቭ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ ኢትዮጵያና አዘርባጃን የጋራ ሉኣላዊነትና የግዛት አንድነትን ያከበረ የአጋርነት ግንኙነት አላቸው ብለዋል።

ያም ብቻ ሳይሆን በአንድ አገር የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ አለመግባት የሚለውን ዓለም ዐቀፍ የአገራት ግንኙነት መርህንም ከግምት ያስገባ ግንኙነት መሆኑን ጠቁመዋል።

አዘርባጃን ኢትዮጵያ መሥራች የሆነችበትን ዓለም ዐቀፍ የገለልተኛ አገራት ንቅናቄ የወቅቱ ሊቀ መንበር መሆኗን አንስተው አገራቸው በዚህኛው ሚና እነዚህን መርሆዎች እንደምታጠናክር ገልጸዋል።

በሁለቱ አገራት መካከል በዓለም ዐቀፍ ጉዳዮች ላይ ያለው አጋርነትም የተጠናከረ መሆኑን ገልጸው ኢትዮጵያ ለአዘርባጃን ለሠጠችው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።

ዓለም ዐቀፍ የዜና አውታሮች አዘርባጃንን በተመለከተ በተለያዩ ጊዜያት ሐሰተኛ መረጃዎች ማሰራጨታቸውን ጠቁመው ይህንንም ዜጎቿ በጋራ ቆመው ማለፋቸውን ተናግረዋል።