የኢትዮጵያን ሕዝብ በመጨፍጨፍ ከዓላማው ማሰናከል እንደማይቻል ታሪክ ምስክር ነው – ፕሮፌሰር ሹመት ሲሻኝ የታሪክ ተመራ

 

በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ከፍተኛ የታሪክ ተመራማሪ እና መምህር ፕሮፌሰር ሹመት ሲሻኝ

የካቲት 12/2013 (ዋልታ)- ኢትዮጵያውያንን በመግደል ከዓላማቸው ማሰናከል እና ድል መቀዳጀት እንደማይቻል ታሪክ ምስክር መሆኑን ከፍተኛ የታሪክ ተመራማሪ ገለጹ።

በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ከፍተኛ የታሪክ ተመራማሪ እና መምህር ፕሮፌሰር ሹመት ሲሻኝ እንደገለጹት፣ በበርካታ ሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ያለቁበትና በወራሪው የጣሊያን ወታደሮች የተፈጸመው የካቲት 12 ቀን 1929 ዓ.ም ጭፍጨፋ በሕዝቦች ዘንድ ሽብር በመፍጠር ድልን የመቀዳጀት ዓላማ የነበረው ነው።

ድርጊቱን በቅርቡ በጽንፈኛው የህወሓት ቡድን የተቀነባበረውን የማይካድራው የዘር ጭፍጨፋም ከየካቲት 12ቱ ጭፍጨፋ ጋር በዓላማ ደረጃ ያላቸውን ተመሳሳይነት እንዳለው የጠቆሙት ፕሮፌሰር ሹመት ፣ እነዚህ ሁለት ድርጊቶች ያነገቡትን ዓላማ ያላሳኩ እና ውጤታቸውም ከታሰበው በተቃራኒ መሆኑን ገልጸዋል።

የየካቲት 12ቱ ጭፍጨፋ ዋነኛ ዓላማ ሕዝቡን ለማስፈራራትና ትግሉን ያስቀጥላሉ ተብለው የታመነባቸው ክፍሎች በማጥፋት የጣሊያንን ተቀባይነት ለማረጋገጥ እንዲሁም የኢትዮጵያውያንን ትግል ጨርሶ ለማዳፈን ያለመ መሆኑን ጠቁመዋል ፕሮፌሰር ሹመት፡፡

በተመሳሳይ መታወቂያ እና ቋንቋ እየተለየ ዜጎች የተጨፈጨፉበት የማይካድራው ጥቃት በተጨፍጫፊው ሕዝብ ዘንድ ፍርሃትና ሽብር በመፍጠር ድሉን ለመንጠቅ የተደረገ ጥረት መሆኑን አመልክተዋል።

ከምንም በላይ ሁለቱም ክስተቶች አንድ የሚያደርጋቸው ደግሞ ሕዝብ በማንነቱ ተለይቶ የተገደለባቸው ሁነቶች ከመሆናቸውም በተጨማሪ ሁለቱ ዘግናኝ ጭፍጨፋዎች የመነጩት ከፈጻሚዎቹ ተስፋ የመቁረጥ ስሜት ነው ብለዋል ሲል ኢፕድ ዘግቧል።