የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም የማስጠበቅ፣ የልማትና የሰላም ግንባታ ጉዳይ የጋራ ሀገራዊ አጀንዳችን ሆኖ ይቀጥላል – የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት

መስከረም 6/2016 (አዲስ ዋልታ) የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም የማስጠበቅ፣ የልማትና የሰላም ግንባታ ጉዳይ የጋራ ሀገራዊ አጀንዳችን ሆኖ ይቀጥላል ሲሉ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሰቢ ደስታ ዲንቃ ተናገሩ።

በርካታ የዓለም አገራት የፖለቲካና የፖሊሲ አተገባበር ልዩነት ቢኖሯቸውም የብሄራዊ ጥቅማቸውና የልማታቸው ጉዳይ ግን ለድርድር የሚቀርብ አይሆንም።

በኢትዮጵያም ለውጡን ተከትሎ እየታየ ያለው የልማትና የሀገር ግንባታ ሂደት በጥሩ ማሳያነት የሚጠቀስ መሆኑን በርካቶች ያነሳሉ።

የኢትዮጵያዊያን የጋራ አሻራ ያረፈበት ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የፕሮጀክት አፈፃፀም ስኬትም የዚሁ ማሳያ ተደርጎ ይወሰዳል።

የግድቡ ግንባታ ሂደት በጥሩ ሁኔታ ቀጥሎ ጳጉሜን 5 ቀን 2015 ዓ.ም አራተኛውና የመጨረሻው የውሃ ሙሌት ተከናውኖ በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ይፋ መደረጉ ይታወቃል።

በመሆኑም የህዳሴ ግድብን ጨምሮ ሌሎችም የልማት ክንውኖች የሀገር ግንባታ መሰረቶች ሆነው ለትውልድ የሚሻገሩ ይሆናሉ።

በእነዚህና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሰቢ ደስታ ዲንቃ፤ የሀገር ልማት ጉዳይ የዜጎች ሁሉ የጋራ አጀንዳ ሆኖ መቀጠል ያለበት ስለመሆኑ ይናገራሉ።

የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም የማስጠበቅ፣ የልማትና የሰላም ግንባታ ሂደት ያለ ልዩነት የምንተገብራቸው የጋራ አጀንዳዎች ሆነው ይቀጥላሉ ብለዋል።

በአስደናቂ ስኬት የቀጠለው የህዳሴ ግድብ ግንባታም የሀገራችን የልማት ስኬት ማሳያ፣ የጋራ ሃብትና የአንድነታችን ማሳያ ነው ሲሉ ተናግረዋል።

በመሆኑም ማናችንም የፓለቲካ አስተሳሰብ ልዩነቶች ቢኖሩንም በሀገራዊ ልማት፣ ዘላቂ ሰላምና አንድነታችንን ማስጠበቅ ላይ ልንደራደር አይገባም ብለዋል።

በተለይም የፓለቲካ ፓርቲዎች በህዳሴ ግድብና በሌሎችም ሀገራዊ የልማት እቅዶች ላይ አጋዦች እንጂ ፈፅሞ የአፍራሽነት ሚና ሊኖረን አይገባም ነው ያሉት።

የፓለቲካ ፓርቲ አመራሮች የህዳሴ ግድብ የግንባታ ሒደትን በቅርቡ የመጎብኘት እድል እንደነበራቸው አስታውሰው ጉብኝታቸው ለበለጠ ድጋፍና ትብብር ያነሳሳቸው መሆኑን ገልጸዋል።

የግድቡ ግንባታ እስከሚጠናቀቅ ድረስም የጋራ ምክር ቤቱ ድጋፍና እገዛ የማይለይ መሆኑን ሰብሳቢው አረጋግጠዋል።

የቀጣይ ስራዎቻችን ከኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ባሻገር ለማህበራዊና የፖለቲካ መስተጋብሮች ቁርኝት ይበልጥ አጋዥ ሆነው ሊቀጥሉ ይገባል ነው ያሉት።