“የኢትዮጵያን እናምርት” በሚል መሪ ሀሳብ የኢንዱስትሪውን ዘርፍ ተወዳዳሪ ለማድረግ እየተሠራ ነው

ሚያዝያ 9/2014 (ዋልታ) “የኢትዮጵያን እናምርት” በሚል መሪ ሀሳብ የውጤታማ ሀገራት ተሞክሮ ተቀምሮበት አምራች ኢንዱስትሪው ተወዳዳሪ እና ውጤታማ እንዲሆን እየተሠራ መሆኑን የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል ተናገሩ፡፡

ሚኒስትሩ ይህንን ያሉት የፌዴራል እና የክልል ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች በደብረ ብርሃን ከተማ የሚገኙ ነባር ኢንቨስትመንቶችን በጎበኙበት ወቅት ነው፡፡

ለአምራች ኢንዱስትሪው ትኩረት በመስጠት አዳዲስ ኢንዱስትሪዎችን በመሳብ፣ ነባሮቹን በማጠናከር ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የተሻለ የሀገር ምጣኔሃብት ለመገንባት እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል።

በበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት ከአምራች ኢንዱስትሪው ምርት ለውጪ ገበያ በማቅረብ 390 ሚሊየን ዶላር ገቢ ተገኝቷል። ይህም የእቅዱን 87 በመቶ መፈፀሙን ነው ያመላከቱት።

በዘርፉ ያሉ ችግሮችን መቅረፍ እና ምቹ ሁኔታዎችን በማመቻቸት ሀገሪቷ ከዘርፉ የምታገኘውን ገቢ ለማሳደግ የሚመለከታቸው አካላት በትጋት ሊሠሩ ይገባል ማለታቸውን አሚኮ ነው የዘገበው።