ጥቅምት 22/2017 (አዲስ ዋልታ) የኢትዮጵያን የሁለትዮሽ እና የባለብዙ ወገን የዲፕሎማሲ ግንኙነቶች የበለጠ ለማጠናከር በጠንካራ ቅንጅታዊ አሠራር መንቀሳቀስ እንደሚገባ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር) ገለጹ።
ሚኒስትሩ በመላው ዓለም ከሚገኙ የኢትዮጵያ ኤምባሲዎች እና ቆንስላ ጄኔራል ጽሕፈት ቤቶች ኃላፊዎች ጋር በበይነ መረብ ትውውቅ አድርገዋል።
አምባሳደሮች እና ዲፕሎማቶች ወቅታዊውን የዓለም ጂኦ-ፖለቲካ አካሄድ ከግንዛቤ ውስጥ በማስገባት የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም በተሻለ ሁኔታ ለማስጠበቅ ትኩረት ሰጥቶ መንቀሳቀስ እንደሚገባ አሳስበዋል።
አምባሳደሮች እና ዲፕሎማቶች በበኩላቸው ከመቼውም ጊዜ በበለጠ የአገራቸውን ብሔራዊ ጥቅም ለማስጠበቅ በትጋት እንደሚንቀሳቀሱ መግለጻቸውንም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል።