የኢትዮጵያዊያን ቀን የጉለሌ ክፍለ ከተማ

ጳግሜ 1/2013 (ዋልታ) – ለኢትዮጵያ ክብር እቆማለሁ ፤ ቆሜ እዘምራለሁ በሚል መርህ ቃል የኢትዮጵያዊያን ቀን በጉለሌ ክፍለ ከተማ ተከበረ፡፡
ያለፉት ሁለት አስርት ዓመታት ኢትዮጵያዊነት የኢትዮጵያዊያን ማንነት መሆኑ ቀርቶ ዜጎች በዘር የሚከፋፈሉበት፣ እርስ በርሳቸው የሚጠራጠሩበት እና የሚያፍሩበት ሆኖ መቆየቱን ነው የበዓሉ ተካፋዮች የተናገሩት።
ነገር ግን ኢትዮጵያዊነት ኃይል በመሆኑ ይህን እኩይ አስተሳሰብ ከምንጩ አሸንፎት ለዘመናት ሲነፈቅ የነበረው ኢትዮጵያዊነት ስለመምጣቱ በጳጉሜ 1 ቀን 2013 ዓ.ም የሚከበረው የኢትዮጵያዊያን ቀን ማሳያ መሆኑን ገልፀዋል።
ኢትዮጵያዊነት ውበት፣ ጉልበት እና የጀግንነት ተምሳሌነት ነው ያሉት የክፍለ ከተማው ዋና ስራ አስፈፃሚ አባወይ ዮሐንስ፣ ይህን ውበት እና አንድነት ለመናድ እየሰሩ ያሉ ባንዳዎችን በጀግንነት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ከኢትዮጵያ ላይ ለመደምሰስ ሁሉም ኢትዮጵያዊያን ካለ አንዳች ልዩነት መዋጋት አለበት ብለዋል።
ኢትዮጵያዊነት የኢትዮጵያዊያን ኩራት በመሆኑ የዛሬውን የኢትዮጵያዊያን ቀን ሲከበር ከጫፍ እስከ ጫፍ የኢትዮጵያዊያንን አንድነት የበለጠ የሚያጠናክር ቀን እንደሆነም ገልጸዋል።
ኢትዮጵያን እና ኢትዮጵያዊያንን ፈተና ተጋርጦብን ይገኛል ያሉት የክፍለ ከተማው ነዋሪዎች እና ሰራተኞች ይህንን ለመሻገር ሁሉም በያለበት ኢትዮጵያን ለማሻገር መስራት እንዳለበት አሳስበዋል።
በሚልኪያስ አዱኛ