የኢትዮጵያዊያን የምክክር ሂደት በስኬት እንዲጠናቀቅ የንግዱ ማኅበረሰብ ሁለንተናዊ ድጋፍ እንዲያደርግ ጥሪ ቀረበ

መስፍን አርዓያ (ፕ/ር)

ሐምሌ 27/2014 (ዋልታ) የኢትዮጵያዊያን የምክክር ሂደት ያለማንም የውጭ ጣልቃ ገብነት በስኬት እንዲጠናቀቅ የንግዱ ማኅበረሰብ የገንዘብና ሌሎች አስፈላጊ ድጋፎችን እንዲያደርግ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ጥሪ አቀረበ።

የኮሚሽኑ ሰብሳቢ መስፍን አርዓያ (ፕ/ር) ኮሚሽኑ ባለፉት አምስት ወራት ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይቶችን በማድረግ ለምክክር የሚጠቅሙ ግብዓቶችን እየሰበሰበ ነው ብለዋል።

ሀገራዊ ምክክሩ የኢትዮጵያዊያን አጀንዳ በመሆኑ የጋራ መግባባትን በመፍጠር ዘላቂ ሰላምና ልማት እውን ለማድረግ ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።

በአንድ አገር ውስጥ ሰላም ከሌለ የኢኮኖሚም ይሁን ማኅበራዊ እንቅስቃሴ የሚስተጓጎል በመሆኑ በተለይም የንግዱ ማኅበረሰብ ዋነኛ ተጎጂ ይሆናል ነው ያሉት።

ሀገራዊ ምክክሩ ሰፊና የንግዱን ማኅብረሰብ ጨምሮ ሁሉንም አካታች በሆነ መልኩ የሚከናወን አገራዊ አጀንዳ መሆኑን ተናግረዋል።

ለአገራዊ ምክክሩ ስኬት የገንዘብ ድጋፍን ጨምሮ ሁለንተናዊ እገዛ የሚጠይቅ በመሆኑ በተለይም የንግዱን ማኅበረሰብ የነቃ ተሳትፎ ይጠይቃል ብለዋል።

የኢትዮጵያዊያን አጀንዳ በኢትዮጵያዊያን ገንዘብና ጉልበት እንዲሁም እውቀት መመራት ስላለበት ኮሚሽኑ የውጭ ተቋማትን የገንዘብ እርዳታ እንደማያማትርና በአዋጅም የተከለከለ መሆኑን ጠቁመዋል።

በመሆኑም በገንዘብ እጥረት ምክንያት አጀንዳው በውጭ ኃይሎች እንዳይጠመዘዝ የንግዱ ማኅበረሰብ የገንዘብና የጉልበት ድጋፍ ወሳኝ መሆኑን አንስተዋል።

ኮሚሽኑና የንግዱ ማኅበረሰብ በሀገራዊ ምክክሩ ውስጥ ሊካተቱለት የሚገቡ አጀንዳዎችን በተመለከተ በቀጣይ ውይይት እንደሚያደርግ የጠቀሱት የኮሚሽኑ ሰብሳቢ በአጀንዳዎቹ ላይ መግባባት ላይ እንደሚደረስም ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ እና በዙሪያዋ ያለው ቀጣና ሰላም የደፈረሰበት አካባቢ በመሆኑ ችግሩን ለመፍታት ምክክርና ውይይት እንደሚያስፈልግም ጠቅሰዋል።

ኢትዮጵያ የጀመረችው ሀገራዊ ምክክር ለቀጣናው ተምሳሌት እንደሚሆን ጠቁመው የንግዱ ማኅበረሰብ በአካባቢው ሀገራት ያለውን ትስስር ተጠቅሞ የምክክርን አስፈላጊነት እንዲያጎላ መጠየቃቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW