የኢትዮጵያ ሀገር በቀል እውቀት ማዕከል ተመሰረተ

ግንቦት 1/2014 (ዋልታ) የኢትዮጵያ ሀገር በቀል እውቀት በትምህርት ደረጃ ለሁሉም ማኅበረሰብ ተደራሽ እንዲሆን ዓላማ ያደረገው የኢትዮጵያ ሀገር በቀል እውቀት ማዕከል ተመስርቷል፡፡
የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) ሀገር በቀል እውቀትን በትምህርት ደረጃ ለሁሉም ማኅበረሰብ ተደራሽ እንዲሆን ዓላማ በማድረግ ለመጪው ትውልድ ጠቃሚ ልምዶችን ለማስተላለፍ እንዲቻል የኢትዮጵያ ሀገር በቀል እውቀት ማእከል መመስረቱ የሚያበረታታ ተነሳሽነት ነው ብለዋል፡፡
ቻይና፣ ታይላንድና ጃፓን የመሳሰሉት ሀገራት በሳይንስና ምርምር አሁን ለደረሱበት የእድገት ደረጃ መሰረታቸው ሀገር በቀል እውቀቶች መሆናቸውን አመላክተዋል፡፡
ሀገር በቀል እውቀቶች እንዳይጠፉ መጠበቅ፣ እውቀትን ለትውልዱ በሚገባ በማስተማር ተጠቃሚ ማድረግ፣ የግብረገብ ትምህርትን በስፋት ማስተማር፣ ስለ እፅዋት ጥበቃና እንክብካቤ፣ ስለ መድኃኒት እጽዋት፣ ስለ ጥንታዊ ስእሎች አሳሳል፣ ስለ ቀለማት አቀማመም እና ስለ ጂዎሎጂ የድንጋይ ጥበብ ማስተማር ሀገራችን የያዘችውን የብልጽግና ጎዳና የሰመረ ለማድረግ የሚያግዝ ነው ተብሏል፡፡
የታሪክ ምሁር የሆኑት ፍቅሬ ቶሎሳ (ፕ/ር) ሀገር በቀል ዕውቀቶችን በሚገባ ባለመጠቀማችን፤ ባለማሳደጋችንና ለትውልድ ባለማስተላለፋችን በቀላሉ የውጭ ተጽዕኖ ውስጥ እንድንወድቅና ውስጣዊ ማንነታችንን እንዲወሰድብን በር ከፍቷል ብለዋል፡፡
የተወሰደብንን ማንነት መልሰን ኢትዮጵያዊ ትምህርትና ዕውቀት ለማበልጸግና ምሉዕ እንዲንሆን የኢትዮጵያ ሀገር በቀል ዕውቀት ትምህርት ማዕከል ወሳኝ ነው ማለታቸውን የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ አመላክቷል፡፡