የኢትዮጵያ ሕዝብ ሁሌም የሰራዊቱ ደጀን በመሆኑ የከበረ ምስጋና ይገባዋል– የመከላከያ ሰራዊት አባላት

ሐምሌ 22/2014 (ዋልታ) የኢትዮጵያ ሕዝብ በአገር ሉዓላዊነት ላይ የተደቀነን አደጋ በመመከት ሁሌም የሰራዊቱ ደጀን በመሆኑ ምስጋና እንደሚገባው የመከላከያ ሰራዊት አባላት ተናገሩ፡፡

‘ካጣነው ይልቅ የተሰጠን ይበልጣል’ በሚል በትናትናው እለት በአገር አቀፍ ደረጃ የምስጋና መርኃ ግብር ተካሂዷል፡፡

በዚህም የመንግሥት ተቋማት እንደየዘርፋቸው ምስጋና ለሚገባቸው ምስጋናን ያቀረቡ ሲሆን ኢዜአ ያነጋገራቸው የመከላከያ ሰራዊት አባላትም ለሰራዊቱ ደጀን የሆነውን የኢትዮጵያን ሕዝብ አመስግነዋል፡፡

በአገር መከከያ ሚኒስቴር የመከላከያ ሥነ-ልቦና ግንባታ ዋና ዳይሬክቶሬት አባል ሻለቃ አስቻለው ሌንጫ ”የኢትዮጵያን ሕዝብ አመስግኖ ማብቃት አይቻልም” ብለዋል።

የኢትዮጵያ ሕዝብ በብሔራዊ ክብሩ፣ በሉዓላዊነቱና በነጻነቱ የማይደራደር መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሕዝብ ለአገር መከላከያ ሰራዊት ደጀንነቱን ደግሞ ደጋግሞ በተግባር ያሳየና ያስመሰከረ መሆኑንም እንዲሁ።

ኢትዮጵያ የሉዓላዊነት አደጋ በተደቀነባት ጊዜ የውጊያ ቀጣና ድረስ በአካል በመሄድ ይህንኑ በተግባር አረጋግጧል፤ ለዚህም ትልቅ ምስጋና ይገባዋል ነው ያሉት።

በተመሳሳይ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ባሻገር የአገር መከላከያ ሰራዊት አባላት ወላጆች ምስጋና እንደሚገባቸውም ነው የጠቀሱት፡፡

ልጆቻቸው የአገርን ክብርና ዳር ድንበር እንዲያስከብሩ ትልቅ ውለታ የዋሉ በመሆኑ ሊመሰገኑ ይገባል ነው ያሉት።
ሌላኛው የዚሁ ዳይሬክቶሬት አባል የሆኑት ሻለቃ ዴቢሶ ዳፋም የኢትዮጵያ ሕዝብ ትልቅ ምስጋና እንደሚገባው ተናግረዋል።
”እኛም ለእሱ ቆመናል፤ እሱም ለእኛ ደግሞ ደጀን ሆነው በአንድነት አገራችንና የአገራችንን ክብር ከፍ እያደረግን ነው” በማለት ገልጸዋል።
በተጨማሪ የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ በዓለም አደባባይ ክፍ ብሎ እንዲውለበለብ ላደረጉት አትሌቶች ምስጋና አቅርበዋል፡፡
”ስፖርተኞቻችን የማንነታችን መገለጫዎች ናቸው” የሚሉት ሻለቃ ዴቢሶ ”የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ከፍ ብሎ ሲውለበለብ እንደማየት የሚያስደስት ነገር የለም” ብለዋል።