የኢትዮጵያ መንግሥት ‘ኤችአር 6600’ ረቂቅ ሕግ እንዳይጸድቅ ጠንካራ የዲፕሎማሲ ሥራ መሥራት እንደሚገባ ተጠቆመ

መጋቢት 10/2014 (ዋልታ) የኢትዮጵያ መንግሥት ‘ኤችአር 6600’ ረቂቅ ሕግ እንዳይጸድቅ ጠንካራ የዲፕሎማሲ ሥራ መሥራት እንዳለበት በአሜሪካ የሚኖሩ ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ገለጹ።

‘ኢትዮጵያ ስታብላይዜሽን ፒስ ኤንድ ዴሞክራሲ አክት’ ወይም ‘ኤችአር 6600’ በአሜሪካ ኮንግረስ የውጭ ጉዳዮች ኮሚቴ ውይይት እንደተደረገበት ይታወቃል።

እንደኢዜአ ዘገባ በአሜሪካ የሚኖሩ ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ‘ኤችአር 6600’ ኢትዮጵያን ለመጉዳትና ለማዳከም የተዘጋጀ ረቂቅ መሆኑን ገልጸዋል።

በተለይም ኢትዮጵያ አሜሪካን ጨምሮ ከዓለም ዐቀፍ የፋይናንስ ተቋማት ብድር እንዳታገኝ፣ የመሳሪያ ግዢ እንዳትፈጽም የሚከለክልና ጫና የሚያሳድር መሆኑን ተናግረዋል።

በረቂቅ ሕጉ በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ የሚናገሩ ሰዎች መልዕክቶቻቸው በማኅበራዊ ትስስር ገጾች እንዳይተላለፉ እንደሚያደርግና ይህም ዳያስፖራው የአገሩን ጥቅም ለማስጠበቅ የሚያከናውነው ሥራ ላይ ተጽዕኖ እንደሚያሳድር አመልክተዋል።

በጥቅሉ ረቂቅ ሕጉ ዳያስፖራው በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ የሚያደርገውን ተሳትፎ የማስቆም ዓላማ ያለው እንደሆነም የኢትዮ-አሜሪካ የዜጎች ምክር ቤት ተሟጋች (አድቮኬት) አስኳል ተፈሪ እና በቨርጂኒያ የፑሽስታርት ሚዲያ ሪፖርተር ቤቲ ተከስተ የተባሉ ትውልደ ኢትጵያዊያኑ ያስረዱት።