“የኢትዮጵያ መንግስት ርሃብን እንደመሳሪያ ተጠቅሟል” በሚል ዘ ኢኮኖሚስት ያወጣውን ዘገባ መንግስት እንደሚያወግዝ አስታወቀ

“የኢትዮጵያ መንግስት ርሃብን እንደመሳሪያ ተጠቅሟል” በሚል ዘ ኢኮኖሚስት ያወጣውን ዘገባ መንግስት በፅኑ እንደሚያወግዝ አስታወቀ፡፡

መፅሄቱ በትግራይ ክልል ከተካሄደው የህግ ማስከበርና የህልውና ዘመቻ ጋር በተያያዘ ባወጣው ዘገባ በኢትዮጵያ መንግስት እየተሰራ ያለውን ስራ በተመለከተ የተሳሳተና የተዛባ ፅሁፍ መጻፉን አስታውሷል፡፡

በሰራው ዘገባም “መንግስት በትግራይ ክልል ርሃብን እንደመሳሪያ እየተጠቀመ ነው” ማለቱ ተጠቅሷል፡፡

ከዚሁ ጋር በተያያዘም መንግስት ለመፅሄቱ ግልጽ ደብዳቤ ጽፏል፡፡

በደብዳቤውም የኢትዮጵያ መንግስት ባለፉት ወራት ከ31 ሺህ ሜትሪክ ቶን በላይ ምግብና መድሃኒቶችን በዘመቻው ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች ድጋፍ በማሰባሰብ ወደ ትግራይ ክልል መላኩን አስታውሷል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም በአካባቢው የዜጎችን ደህንነትና ሰላም ለማስጠበቅ ስራዎች መስራቱንም አንስቷል፡፡

ይሁን እንጅ መፅሄቱ በዘገባው የተወሰኑ ምዕራባውያንን እማኝ በማድረግ እርግጠኛ ያልሆነና የተዛባ መረጃ ማውጣቱንም ጠቅሷል፡፡

ከዚህ ጋር ተያይዞም በፅሁፉ “የመንግስትን ህገ መንግስታዊ ግዴታ ማጣጣሉን” በመጥቀስ፥ ጽሁፉ “መንግስት አቅመ ቢስ ነው ወደሚል ስድብ ያዘነበለ” መሆኑንም አውስቷል፡፡

በኢትዮጵያ ሁሉን አቀፍ ማሻሻያዎች እየተደረጉ መሆናቸውን ያነሳው ደብዳቤው በትግራይ ክልል የተካሄደው ህግን የማስከበር ዘመቻ ዋጋ የሚያስከፍል ቢሆንም አስፈላጊ ስለመሆኑም ገልጿል፡፡