“የኢትዮጵያ መንግስት የሱዳን ተቃዋሚዎችን ይረዳል” የሚለው መረጃ መሰረተ ቢስ ነው – አምባሳደር ይበልጣል አዕምሮ

በሱዳን ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ይበልጣል አዕምሮ

መጋቢት 01/2013 (ዋልታ) – በሱዳን ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ይበልጣል አዕምሮ ሱዳን ለሚገኙ የሀገር ውስጥ እና አለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን የትግራይን ክልል ወቅታዊ ሁኔታ አስመልክቶ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸውም ወንድም የሆነው የሱዳን ህዝብ እንደ ጎረቤት ስለ ኢትዮጵያ የውስጥ ሁኔታ ትክክለኛ እና ወቅታዊ መረጃ እንዲደርሰዉ ማድረግ አስፈላጊ በመሆኑ ጋዜጣዊ መግለጫ መዘጋጀቱን ጠቅሰዋል።

አምባሳደር ይበልጣል ሕዋሃት ከመነሻው ጀምሮ በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ ሲያደርስ ስለነበረው ግፍና ዘረፋ፣በሀገር መከላከያ ላይ ስለፈጸመዉ ዘግናኝ ጥቃት፣በማይካድራ ስለፈጸመዉ ዘር ተኮር ጭፍጨፋ፣በክልሉ ወንጀለኞችን ለህግ ለማቅረብ ስለተደረገዉ ጥረት፣ሰባዊ እርዳታ ለተረጂዎች እንዲደርስ እየተደረገ ስላለዉ ጥረት፣በሕዋሃት የፈረሰዉን መሰረት ልማት መልሶ ለመገንባት እንዲሁም የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ላይ ስለተጀመረው የምርመራ ሂደት በዝርዝር አስረድተዋል።

መንግስት የትግራይ ሕዝብ ሙሉ በሙሉ ወደ መደበኛ ሕይወቱ እንዲመለስ ሁለገብ ጥረት እያደረገ ባለበት ወቅት በዉጭ ሀገር የሚኖሩ የሕዋሃት ደጋፊዎች እና አንዳንድ ሚዲያዎችና መንግስታት በትግራይ በሰላማዊ ማህበረሰብ ላይ ወንጀል እንደፈጸመ አድርገዉ የተዛባ መረጃ በማሰራጨት ኢትዮጵያ ተገቢ ያልሆነ ጫና እንዲደርስባት የተቀነባበረ ሁለገብ ዘመቻ የተከፈተባት መሆኑን ለጋዜጠኞቹ ገልፀዋል።

ከዚህ አንጻር ለኢትዮጵያና ኢትዮጵያዉያን ቆሚያለሁ የሚል ካለ ጉዳዩን ከመሰረቱ በአግባቡ በመረዳት የመንግስትን ጥረት መደገፍ እንደሚኖርበት፣ከዚህ ዉጭ የሚደረግ አፍራሽ እንቅስቃሴ ለኢትዮጵያ የማይጠቅም በኢትዮጵያ ሕዝብና መንግስት ዘንድም ተቀባይነት የሌለዉ መሆኑን ተናግረዋል።

“የኢትዮጵያ መንግስት የሱዳን ተቃዋሚዎችን ይረዳል” ስለሚባለዉ ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸዉ ጥያቄ በሠጡት ምለሽ “የቀረበዉ ክስ መሰረት ቢስ ነዉ፣የኢትዮጵያ መንግስት የሰራዉን ቤት አያፈርስም፣አሁን በሱዳን ዉስጥ የምናየዉ ሠላም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ እና የኢትዮጵያ መንግስት የደከሙለት ነዉ” ሲሉ አስረድተዋል።

ከስደተኞች ጋር ተያይዞ ለተነሳዉ ጥያቄ ስደተኞቹን ለመመለስ ከሱዳን መንግስተ ጋር ምክክር እየተደረገ መሆኑናንና ከዚህ ጋር ተያይዞ የተወሰኑ ስደተኞች ተመዝግበዉ ለመመለስ እየተጠባበቁ እንደሆነ አስግንዝበዋል።