የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ማሻሻል በሚገባቸው ጉዳዮች ዙሪያ እየተወያየ ነው

ሰኔ 22/2013 (ዋልታ) – የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ማሻሻል በሚገባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት እያካሄደ ይገኛል፡፡

በውይይቱ ለረጅም ዓመታት የሰሩ የዘርፉ ባለሙያዎች በመገናኛ ብዙሃን ወቅታዊ ሁኔታ ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን በማንሳት መፍትሄ የሚሆኑ ሀሳቦች ላይ ትኩረት አድርገዋል፡፡

በሙያው ለ50 ዓመታት የሰሩት አቶ ማረጉ በዛብህ የኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙሃን ታሪካዊ ዳራ በማንሳት ዘርፉ የመንግስት ፕሮፓጋንዳ መሳሪያ ሆኖ ሲያገለግል መቆየቱን ገልጸው፣ አሁንም ሙሉ ለሙሉ ነፃ አለመውጣቱን እንደ ችግር አንስተዋል።

የፕሬስ ነፃነት በብዛት አለመታየቱ፣ በማህበረሰብ ጉዳዮች ላይ አጀንዳ ቀርፆ ህብረተሰቡን ማንቃት ላይ ቀጣይነት ያለው ስራ አለመሰራቱ እና ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ተደራሽ አለመሆን እንደ ችግር ተነስቷል።

ሙያተኝነት የዘርፉ ችግር ነው ያሉት ጋዜጠኛ መዓዛ ብሩ፣ በተለይ የሚዲያ ተቋማት እና የስልጠና ተቋማት አብሮ የመስራት ልምድ አለመኖር ሙያውን በተግባር እንዳይታገዝ አድርጎታል ብለዋል።

ሚዳያ ካለምንም ወገንተኝነት የቆመ መሆን አለበት ቢባልም አለመተግበሩ እና የማህበራዊ ትስስር ገጾች መበራከት ለመገናኛ ብዙሃን ፈተና መሆኑንም በምክንያትነት አንስተዋል።

ከጊዜ ወደ ጊዜ ዘርፉ እየተዳከመ ከመምጣቱ የተነሳ ዘርፉን ማነቃቃት እና የባለሙያውን ብቃት ለማሳደግ የሚሰራ በሚኒስቴርም ሆነ በሌላ ደረጃ የራሱ የሆነ ባለቤት ሊኖረው ይገባልም ተብሏል።

የህትመት ሚዲያን የተሻለ በማድረግ ባለሙያውን በየዘርፉ በቂ እውቀት እንዲኖረው በተለያዩ ስልጠናዎች ማብቃት ያስፈልጋል ነው የተባለው።

(በትዕግስት ዘላለም)