የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ምክር ቤት ጠቅላላ ጉባዔውን እያካሄደ ነው

ጥር 24/2014 (ዋልታ) የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ምክር ቤት ዓመታዊ ጠቅላላ ጉባዔ እያካሄደ ይገኛል፡፡
የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክር ቤቱ አስፈላጊውን እንቅስቃሴ እንዳያደርግ ከፍተኛ ተግዳሮት እንደሆነበት የምክር ቤቱ ሰብሳቢ ትዕግስት ይልማ ገልፀዋል፡፡
ምክር ቤቱ የሚያጋጥሙትን ችግሮች ተቋቁሞ ራሱን የማደራጀት ሥራ ማከናወኑንም ሰብሳቢዋ ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር መሀመድ እድሪስ በበኩላቸው አንዳንድ የውጭ መገናኛ ብዙኃን አሸባሪው የትሕነግ ቡድን በኢትዮጵያ ላይ የጋረጠበትን ፈተና በመደበቅ ሀሰተኛ መረጃዎችን እና ጥላቻን ሲያሰራጩ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ግን እውነታውን ለዓለም ማኅበረሰብ በማሳወቅ በኩል ከፍተኛ ሚና መጫወታቸውን ገልጸዋል፡፡
የኮቪድ-19 ወረርሽኝን አስከፊነት በማኅበረሰቡ ዘንድ ከፍተኛ ግንዛቤ በመፍጠር እና በሀገራዊ ምርጫ ጊዜ ትክክለኛ መረጃን በአስፈላጊው ሁኔታ በማሰራጨት በኩል በርካታ ተግባራት መከናወናቸውንም ተናግረዋል፡፡
ምክር ቤቱ ነፃነቱ የተጠበቀ እና ኃላፊነቱን የሚወጣ ሚዲያ በሀገሪቱ እንዲኖር በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝም ተመልክቷል፡፡
በውይይቱ የተለያዩ የሚዲያ ኃላፊዎች፣ የምክር ቤቱ አባላት እና ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ይገኛሉ፡፡
በአመለወርቅ መኳንንት