የኢትዮጵያ ምርት ገበያ በአራት ወራት ከ51 ሺሕ ሜትሪክ ቶን በላይ ምርቶች ማገበያየቱን አስታወቀ

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ

ኅዳር 8/2014 (ዋልታ) ባለፉት አራት ወራት ከ51 ሺሕ ሜትሪክ ቶን በላይ የግብርና ምርቶችን በ4 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር ማገበያየቱን የኢትዮጵያ ምርት ገበያ አስታወቀ፡፡

ከዚህ ውስጥ 17 ሺሕ 690 ቶን ቡና፣ 15 ሺሕ 445 ቶን ሰሊጥ፣  3 ሺሕ 24 ቶን ነጭ ቦሎቄ፣ 4 ሺሕ 731 ቶን አኩሪ አተር፣ 3 ሺሕ 368 ቶን አረንጓዴ ማሾ፣ 1 ሺሕ 904 ቶን ዥንጉርጉር ቦሎቄ፣ 215 ቶን ቀይ ቦሎቄና አምስት ቶን የርግብ አተር አገበያይቷል።

በሐምሌ 2013 ዓ.ም የአንድ ኩንታል አማካይ የግብይት ዋጋ 7 ሺሕ 235 ብር የነበረ ሲሆን በጥቅምት ወር 2014 ዓ.ም 7 ሺሕ 841 ብር ሆኗል ተብሏል፡፡ ይህም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ዋጋው በእጥፍ ጨምሯል።

በሌላ በኩል ጥቁር አዝሙድ፣ ድንብላል፣ አብሽና ቁንዶ በርበሬ እንዲሁም ጓያ ወደ ዘመናዊ የግብይት ሥርዓቱ ስለተካተቱ ከተያዘው የምርት ዘመን አንስቶ ግብይታቸው እንደሚካሄድ ከኢትዮጵያ ምርት ገበያ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡