የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ከ19 ቢሊዮን ብር በላይ ዋጋ ያላቸው ምርቶችን ማገበያየቱን አስታወቀ

ባለፉት ስድስት ወራት 19 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር ዋጋ ያላቸው 320 ሺህ ቶን ምርት ማገበያየቱን የኢትዮጵያ ምርት ገበያ አስታወቀ።

ተደራሽነቱን ይበልጥ ለማስፋት በተለያዩ አካባቢዎች አዳዲስ የግብይት ማዕከላትን ለመክፈት በዝግጅት ላይ እንዳለም ገልጿል።

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ወንድማገኘሁ ነገራ የድርጅቱን የስድስት ወራት የስራ አፈጻጸምን አስመልክተው በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳስታወቁት፣ በ2013 በጀት ዓመት በመጀመሪያው ስድስት ወራ 320,140 ሜትሪክ ቶን ምርት በ19 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር አገበያይቷል።

አፈጻጸሙ ከእቅዱ ጋር ሲነፃፀር በመጠን 99 በመቶ በዋጋ 111 በመቶ ማሳካት ያስቻለ መሆኑን ያመለከቱት ዋና ስራ አስፈጻሚው፣ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር አምስት በመቶ የግብይት ቅናሽ፣ 13 በመቶ የዋጋ ጭማሪ መመዝገቡን አመልክተዋል።

ባለፉት ስድስት ወራት 115 ሺህ ቶን ሰሊጥ ለማገበያየት ታቅዶ ከእቅዱ ከ122 በመቶ በላይ 140 ሺህ ቶን ማገበያየቱን የገለጹት አቶ ወንድማገኘሁ፣ ለግብርና ምርት አቀነባባሪዎች በተከፈተው ልዩ የግብይት መስኮትም 10,592 ቶን አኩሪ አተር በ198 ሚሊየን ብር ማገበያየት መቻሉን አስታውቀዋል።

እንደ ዋና ሥራ አስፈጻሚው ገለጻ ነጭ የርግብ አተር፣ ዥንጉርጉር ቦሎቄና ፒንቶ ቢን ወደ ዘመናዊ የግብይት መድረክ በመግባታቸው ምርት ገበያው የሚያገበያየው ምርት ብዛት 12 ደርሷል።

ጥጥ፣ ቅመማ ቅመምና ጥራጥሬን ጨምሮ ዘጠኝ ተጨማሪ ምርቶችን ወደ ግብይት ለማስገባት የአዋጭነት ጥናት እየተካሄደ እንደሚገኝ ኢፕድ ዘግቧል።