ሚያዝያ 17/2013 (ዋልታ) – በኢትዮጵያ ቦክስ ፌዴሬሽን አዘጋጅነት ከሚያዚያ 13 እስከ 16 በሶማሌ ክልል ጅግጅጋ ከተማ ሁለት ከተማ አስተዳደሮች እና ሶስት ክልሎች የተሳተፉበት የኢትዮጵያ ቦክስ ሻምፒዮና ውድድር አዲስ አበበ ከተማ በሁለቱም ፆታ የዋንጫ አሸናፊ በመሆን አጠናቀቀ፡፡
በሻምፒዮናው አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በ3 ወርቅ እና 2 ነሀስ በማምጣት፣ ድሬዳዋ ከተማ በ2 ወርቅ፣ በ2 ብር እና 2 ነሀስ በማስመዝገብ እንዲሁም አማራ በ1 ወርቅ፣ 3 ብር እና 2 ነሀስ በማስመዝገብ ከ1 እስከ 3ኛ ያለውን ደረጃ ይዘው ማጠናቀቅ ችለዋል፡፡
በውድድሩ ከ1 እስከ 3 ያለውን ደረጃ ይዘው ያጠናቀቁ ተወዳዳሪዎች የወርቅ፣ የብር እና የነሀስ ሜዳሊያ ተሸላሚ ሆነዋል፡፡
በሻምፒዮናው ኮኮብ ተጨዋች በመባል በወንዶች ፍትዊ ጥኡም እና በሴቶች አስናቀች አባይነህ ከአዲስ አበባ ተሽላሚ ሲሆኑ፣ በአሰልጣኝነት አበራ ጌታቸው ከድሬዳዋ እና መስከረም ጮራ ከአዲስ አበባ ተሸላሚ መሆናቸውን ከኢፌዴሪ ስፖርት ኮሚሽን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
በሻምፒዮናው ለተሳተፉ ክልሎች የሰርተፍኬት ሽልማት የተበረከተ ሲሆን፣ ሶማሌ ክልል የፀባይ ዋንጫ አሸናፊ ሆኗል፡፡