የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የዘካ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የማስተዋወቅ ንቅናቄ ጀመረ

መጋቢት 21/2014 (ዋልታ) የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዘካ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የማስተዋወቅ ንቅናቄ ጀመረ፡፡
ባንኩ የሼሪዓ መርህን መሰረት ያደረገ የተሟላ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛል።
ዘካ ከእስልምና እምነት መሰረቶች አንዱ ሲሆን አቅም ያላቸው ግለሰቦች ካፈሩት ሃብት የተወሰነውን በጥሬ ገንዘብ ወይም በዓይነት እምነቱ ዘካ እንዲቀበሉ ለፈቀደላቸው ግለሰቦች የሚሰጥ የግዴታ ክፍያ ነው፡፡
የሃይማኖት አባቶች፣ የባንኩ አመራሮች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት የዘካ ተቀማጭ ሂሳብን የማስተዋወቅ ንቅናቄ ተጀምሯል።
ብዙም ያልተለመደው የዘካ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት በሀገሪቱ ጥሩ እንቅስቃሴ እንዳለው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዝዳንት አቤ ሳኖ ገልፀዋል።
ባንኩ የሼሪአ ኮሚቴ ከማቋቋም ጀምሮ በሁሉም ባንኮቹ የሲቢኢ ኑር አገልግሎት እየሰጠ ሲሆን ለዘካ የሂሳብ አገልግሎትም ባንኩ 109 ቅርንጫፎች እንዳሉት ፕሬዝዳንቱ ተናግረዋል።
የታላቁ የረመዳን የፆም ወር ዋዜማን ያስታወሱት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዝዳንት አቤ ሳኖ እና የባንኩ የሲቢኢ ኑሮ ምክትል ፕሬዝዳንት ኑር ሁሴን የዛካ ሂሳብ አገልግሎትን በይፋ አስተዋውቀዋል።
የባንኩ የሼሪዓ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ መሀመድ ሀሚዲን (ዶ/ር) ዘካ በመካከላችን መተሳሰብንና መተጋገዝን የምናጎለብትበት መልካም እሴታችን በመሆኑ ሕዝበ ሙስሊሙ ሊተገብረው ይገባል ብለዋል።
በደምሰው በነበሩ