የኢትዮጵያ አረንጓዴ አሻራ ልማት የአየር ንብረት ለውጥ ተጽእኖ የመቋቋም ጥረት ሁነኛ ማሳያ ነው

አግነስ ኪጃዚ (ዶ/ር)

ሰኔ 16/2016 (አዲስ ዋልታ) የኢትዮጵያ አረንጓዴ አሻራ ልማት የአየር ንብረት ለውጥ ተጽእኖ የመቋቋም ጥረት ሁነኛ ማሳያ መሆኑን በዓለም ሚቲዎሮሎጂ ድርጅት የአፍሪካ ጽህፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር አግነስ ኪጃዚ (ዶ/ር) ገለጹ።

በአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር የኢትዮጵያን ቀጣይነት ያለው ጥረት በተመለከተ ዋና ዳይሬክተሯ አግነስ ኪጃዚ (ዶ/ር) ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ ዓለም አቀፍ ስጋት በሆነው የአየር ንብረት ለውጥ ተጽእኖ በተለይም የአፍሪካ አገራት በእጅጉ እየተፈተነ መሆኑን ገልጸዋል።

የአየር ንብረት ለውጥ ጉዳትን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት የኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ ልማት አስደናቂ እንቅስቃሴ እየታየበት መሆኑን አንስተዋል።

የኢትዮጵያ አረንጓዴ አሻራ ልማት የአየር ንብረት ለውጥ ተጽእኖ የመቋቋም ጥረት ሁነኛ ማሳያ መሆኑን ጠቅሰው ችግሩን በዘላቂነት ለመቋቋም ዓለም አቀፍ ትብብር ያስፈልጋል ብለዋል።

የዓለም ሚቲዎሮሎጂ ድርጅት የአፍሪካ ጽህፈት ቤት የተጠናከረ የአየር ትንበያ ቅድመ ማስጠንቀቂያ ስርዓትን ለመዘርጋት አባል አገራቱን እየደገፈ መሆኑን ገልጸዋል።

ፈጠነ ተሾመ

የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ዋና ዳሬክተር ፈጠነ ተሾመ የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር የአየር ንብረት ተጽእኖን ለመከላከል የሚያስችል የልማት ማእቀፍ በመሆኑ በልዩ ትኩረት እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።

የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር የአየር ንብረት ለውጥን በመከላከልና ዘላቂ ስርዓተ ምህዳርን ለማስጠበቅ ፋይዳው የጎላ መሆኑ ይታወቃል።

በዚህ ረገድ በተከናወነ ጠንካራ ስራ የኢትዮጵያ የደን ሽፋን አሁን ላይ 23 ነጥብ 6 በመቶ መድረሱን የኢትዮጵያ ደን ልማት አስታውቋል።