የኢትዮጵያ አንድነት በጽንፈኛ ኃይሎች እኩይ ተግባር እንደማይፈርስ የሃይማኖት አባቶች ገለጹ

ሚያዝያ 26/2014 (ዋልታ) በጽኑ አለት ላይ የተገነባው የኢትዮጵያ አንድነት ጽንፈኛ ኃይሎች በጠነሰሱት ሴራና እኩይ ተግባር የማይፈርስ መሆኑን በደቡብ ክልል የጋሞ ዞን የሃይማኖት አባቶች አስታወቁ፡፡

በሃይማኖት ሽፋን በጎንደርና ስልጤ ዞን ወራቤ ከተማ የተፈጸሙ እኩይ ተግባራት ሃይማኖቶችን የማይወክሉና ሊወገዙ የሚገባ መሆኑን የሃይማኖት አባቶቹ ለኢዜአ ተናግረዋል፡፡

የጋሞ ዞን እስልምና ጉዳይ ዋና ፀሐፊ ሼኽ መሃመድ ሁሴን የኢትዮጵያ ሕዝብ አንድነት በጽኑ አለት ላይ የተገነባ በመሆኑ ለብዙ ሺሕ ዓመታት በመከባበርና በመቻቻል አብሮ ሲኖር መቆየቱን አውስተዋል፡፡

የክርስትናና የእስልምና ሃይማኖቶች ተከታዮችም በመከባበር፣ በአንድነትና በፍቅር የኖሩ ወንድማማች ህዝቦች  መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡

“በተለይ በአሁኑ ጊዜ በማኅበራዊ ትስስር ገጾች ሃይማኖትንና ብሔርን ሽፋን በማድረግ ኢትዮጵያን ለማፈራረስ በሚቃጡ እንቅስቃሴዎች መታወክ አይገባም” ያሉት ሼኽ መሃመድ መንግሥት በድርጊቱ የተሰማሩ አካላትን በመከታተል እርምጃ ሊወሰድ እንደሚገባ አመልክተዋል፡፡

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የጋሞና ጎፋ ሀገረ-ስብከት ዋና ፀሐፊና የአርባ ምንጭ ከተማ የሃይማኖት ተቋማት ፎረም ሰብሳቢ መጋቢ ሰናያት ያዕቆብ ደስታ ኢትዮጵያዊያን ከአንድነት ውጭ የሚያዋጣን አንዳች አማራጭ የለም ብለዋል፡፡

መንግሥት በጎንደርና በስልጤ አካባቢ ሴረኞችን በቁጥጥር ስር ለማዋል የሚያደርገው እንቅስቃሴ የሚበረታታ መሆኑን ጠቁመው ሕዝቡ ከመንግሥት ጎን በመሆን ጽንፈኞችን አሳልፎ እንዲሰጥ ጠይቀዋል፡፡

በቀልን በበቀል ለመመለስ ማሰብ ሀገሪቱን ወደማያባራ ቀውስ ውስጥ እንደሚከታትና በድርጊቱም ተጎጂው ሕዝቡ ራሱ በመሆኑ ሁሉም የአካባቢውን ሰላም በመጠበቅ የበኩሉን ሊወጣ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡

“ያለሰላም ሃይማኖት ሊኖር የማይችል በመሆኑ ለአባባቢያችን ሰላም ዘብ በመቆም መንግሥት የሚያደርገውን ተግባር በመተባበር የበኩላችንን እንወጣለን” ሲሉ አስታውቀዋል፡፡

በጋሞ ዞን ሰላምና ፀጥታ መምሪያ የሃይማኖትና እምነት ጉዳዮች አስተባባሪ ሻምበል መስፍን አንዳርጌ በበኩላቸው “በጎንደርና ስልጤ የተከሰተው ድርጊት አስነዋሪና አሳዛኝ ነው” ብለዋል፡፡

ድርጊቱ በሃይማኖታዊ ሽፋን የተፈጸመና ጽንፈኞች የኢትዮጵያን አንድነት በመናድ ለጠላት አሳልፎ ለመስጠት ያደረጉት መሆኑን ሕዝቡ ሊገነዘብ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

እንደ ጋሞ ዞንም  የፀጥታ አካላት ከሕዝቡና ሃይማኖት መሪዎች ጋር በመሆን የአካባቢውን ሰላም ለማስጠበቅ እየተጉ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡