የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለሰባተኛ ጊዜ የአፍሪካ ምርጡ አየር መንገድ ሆኖ ተመረጠ

ሰኔ 17/2016 (አዲስ ዋልታ) ስካይ ትራክስ በለንደን ፌርሞንት ዊንድሶር ፓርክ ባካሄደው የ2024 አየር መንገዶች ሽልማት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለሰባተኛ ጊዜ የአፍሪካ ምርጡ አየር መንገድ ሆኖ ተመረጠ።

ከዚህ በተጨማሪም አየር መንገዱ የአፍሪካ ምርጥ ቢዝነስ ክላስ እና ኢኮኖሚክ ክላስ እንዲሁም በአፍሪካ ለኢኮኖሚ ክላስ ተጓዦች ምርጥ የበረራ ላይ ምግብና መጠጥ አቅራቢነት በጥቅሉ አራት ሽልማቶችን አግኝቷል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈፃሚ መስፍን ጣሰው “የ2024 የዓለም አየር መንገድ ሽልማትን ለሰባተኛ ተከታታይ ዓመት በማግኘታችን ደስተኛ ነን ያሉ ሲሆን በኢትዮጵያ አየር መንገድ ደንበኞችን ያማከለ አዲስ ፈጠራ ለመተግበር ያለን ቁርጠኝነት ለስኬታችን ወሳኝ ነበር ብለዋል።

የተሳፋሪዎችን ምቾትና ቆይታ ከፍ ለማድረግ ዘመኑ ያፈራቸውን የቴክኖሎጂ ውጤቶችን በተከታታይ በመተግበር በአቪዬሽን ኢንዱስትሪው ዘርፍ ግንባር ቀደም ሆነናል” ብለዋል።



ከአፍሪካ የሞሮኮው ሮያል ማሮክ፣ ደቡብ አፍሪካ አየር መንገድ፣ የኬንያና የሩዋንዳ አየር መንገዶች በቅደም ተከተል ከ2ኛ እስከ 5ኛ ደረጃን አግኝተዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከዓለም አየር መንገዶች በ36ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠ ሲሆን አምና ከነበረበት 35ኛ ደረጃው በአንድ ደረጃ ቅናሽ አሳይቷል።

በዘንድሮው የስካይ ትራክስ የአየር መንገዶች ሽልማት አንደኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው የኳታር ኤርዌይስ ሲሆን አየር መንገዱ በ25 ዓመታት ጊዜ ውስጥ ለስምንተኛ ጊዜ ነው ያሸነፈው።

ኳታር ኤርዌይስ በፈረንጆቹ 2023 ደረጃውን በሲንጋፖር ኤርላይንስ ተነጥቆ ሁለተኛ የነበረ ሲሆን ዘንድሮ መልሶ ተረክቧል። ሲንጋፖር ኤርላይንስ ዘንድሮ በሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

በዘንድሮው የአየር መንገዶች ደረጃ የኢምሬትስ አየር መንገድ ሶስተኛ ደረጃን ያገኘ ሲሆን የጃፓኑ ኦል ኒፖን፣ ካቲ ፓሲፊክ ኤርዌይስ፣ ጃፓን ኤርዌይስ፣ ቱርኪሽ ኤርላይንስ፣ ኤቫ ኤር፣ ኤየር ፍራንስና ስዊዝ ኢንተርናሽናል ኤርላይንስ በቅደም ተከተል ከአራተኛ እስከ አስረኛ ደረጃን ይዘው ማጠናቀቃቸውን ከስካይ ትራክስ ድረገፅ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።