የኢትዮጵያ አየር መንገድ በናይጄሪያ ‘ምርጡ አየር መንገድ’ ተባለ

መጋቢት 24/2013 (ዋልታ) – የኢትዮጵያ አየር መንገድ በናይጄሪያ ‘ምርጡ አየር መንገድ’ ተባለ።

በናይጄሪያ የድንቆች ኤክስፖ ማገባደጃ ላይ ለተቋማት በተሰጠ እውቅና የኢትዮጵያ አየር መንገድ ‘የምርጥ ዓለም ዓቀፍ ሽልማት’ አሸናፊ ሆኗል።

የአየር መንገዱ የትራፊክና ሽያጭ ስራ አስኪያጅ ሰናይት አታክልቲ ሽልማቱን ከትሪዳድና ቶቤጎ እና ከጃማይካ አምባሳደሮች እጅ ተቀብለዋል።

አየር መንገዱ ለአገልግሎቱ ዕውቅና በመሰጠቱም አመስግነዋል።

እንደ ኢዜአ ዘገባ ያለፈው ዓመት ፈታኝ እንደነበር አስታውሰው አየር መንገዱ ፈተናውን ለማለፍ የጭነት አገልግሎት በመስጠት የወደፊት እጣ ፈንታውን ብሩህ ማድረጉን ገልጸዋል።

አየር መንገዱ የመንገደኞች ማጓጓዣ አውሮፕላኖችን ወደ ጭነት ማጓጓዣነት በመቀየር መስራቱን አስታውሰዋል።

የጭነት ማጓጓዝ ላይ ትኩረት ማድረግ ከተጀመረበት ያለፈው አንድ አመት ጀምሮ የዓለም የምግብ ፕሮግራምን ጨምሮ ከሌሎች አጋሮች ጋር እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ፡ አሊባባ ፋውንዴሽን፣ የአለም ጤና ድርጅት እና ለጋሽ አገሮች ለአፍሪካ የሰጡትን የኮቪድ-19 መከላከያ ቁሳቁሶችን በውጤታማነት ታጅባ ማሰራጨት መቻሏንም ገልጸዋል።