የኢትዮጵያ አየር መንገድ የጥገና ማዕከሉን ዲጂታላይዝ አደረገ

መስፍን ጣሰው

ግንቦት 18/2014 (ዋልታ) የኢትዮጵያ አየር መንገድ የአውሮፕላን ጥገና ማዕከሉን ”ሀንጋር” ዲጂታላይዝ ማድረጉን ገለጸ።

የጥገና ማዕከሉ ወደ ዲጂታል መቀየሩ አየር መንገዱ በየዓመቱ ለወረቀትና የሰው ኃይል ያወጣው የነበረውን 500 ሚሊዮን ብር ያስቀራል ተብሏል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው እንደገለጹት የአየር መንገዱን የአውሮፕላን ጥገና ማዕከል ዲጂታል ለማድረግ የአራት ዓመት ፕሮጀክት ቀርጾ ሲሰራ ቆይቷል።

የጥገና ማዕከሉ አስካሁን በወረቀት የታገዘ አሰራር እንደነበረው ጠቅሰው አሁን ላይ ሙሉ ለሙሉ ዲጅታላይዝ ወደ ሆነ አሰራር መሸጋገሩን ገልጸዋል።

አዲሱ አሰራር አውሮፕላኖች ከድርጅቱ ሲወጡ፣ የተከራዩ ከሆነም ሲመለሱ ወይም በሌላ መንገድ ሲተላለፉ ሪከርድን ለማስተካከል የሚባክነውን ጊዜ ያስቀረ ስለመሆኑም አብራርተዋል።

የጥገና ማዕከሉን በአውሮፓና ሌሎች የዓለም አገራት ከሚሰጡ አገልግሎቶች ጋር ተወዳዳሪ ለማድረግ የሚያስችሉ አሰራሮች ይዘረጋሉ ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ የኦፕሬሽን ዘርፍ ኃላፊ ረታ መላኩ የጥገና ማዕከሉ ዲጅታላይዝ መሆን ለአሰራር ፍጥነትና ቅልጥፍና የጎላ ሚና ያለው መሆኑን ገልጸዋል።

ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW