ነሐሴ 28/2016 (አዲስ ዋልታ) የኢትዮጵያ አየር መንገድ ኤርትራ ውስጥ ያለውን ገንዘብ ከኤርትራ እንዳያወጣ መከልከሉን ገለጸ።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈፃሚ መስፍን ጣሰው በሰጡት መግለጫ ምክንያቱን ባላወቅነው መንገድ አስመራ ውስጥ ያለን የዶላር ገንዘብ እንዳናወጣ ተከልክለናል ብለዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ኤርትራ ውስጥ የናቅፋ እና የሀርድ ከረንሲ (ዶላር፣ ዩሮ እና መሰል መገበያያዎች) የሂሳብ ደብተር ያሉት ሲሆን የሀርድ ከረንሲውን የሂሳብ ደብተር ሲያንቀሳቅስ እንደነበር ተገልጿል፡፡
ይሁን እንጂ በኤርትራ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን ይህን የሀርድ ከረንሲ የሂሳብ ደብተር እንዳያንቀሳቅስ መከልከሉ በመግለጫው ተጠቁሟል።
የተሰበሰበውን ገንዘብ ማውጣት ካልቻልን በበርካታ ወጪዎች ምክንያት ሥራችንን መቀጠል አንችልም ያሉት ዋና ሥራ አስፈፃሚው በጉዳዩ ላይ ለመነጋገር ብንጠይቅም ፈቃደኛ አይደሉም ሲሉም ገልጸዋል።
አክለውም አየር መንገዱ ገንዘብ ካላገኘ እና እዛ ለሚያስፈልጉ ወጪዎች መጠቀም ካልቻለ በረራ ማቆም ብቸኛ አማራጭ እንደሆነ ተናግረዋል።
ወደ ፊትም ችግሩን በንግግር ለመፍታት ጥረት ይደረጋል ብለዋል።
በማህሌት መህዲ