የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን በሚቋቋምበት ረቂቅ አዋጅ ላይ ለሲቪል ማኅበራት ገለፃ ተደረገ

ታኅሣሥ 15/2014 (ዋልታ) የሚኒስትሮች ምክርቨቤት የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን በሚቋቋምበት አዋጅ ላይ ማኅበረሰቡን ለማሳተፍ ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት ለሲቪል ማኅበራት ገለፃ ተደረገ፡፡
ኮሚሽኑን ማቋቋምን በተመለከተ ከሲቪል ማኅበራት ጋር ውይይት የተካሄደ ሲሆን፤ የሥራ እና ክህሎት ሚኒስትር ሙፍሪያት ካሚል እና የከተማ እና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ በአዋጁ ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
የአገራዊ ምክክር አስፈላጊነት፣ ዓላማ፣ ለአገራዊ ምክክር አስፈላጊ ነገሮች፣ የሌሎች አገራት ተሞክሮ እንዲሁም የኮሚሽነሮች አመራረጥ እና መሰረታዊ መስፈርቶች ላይ መነሻ ሐሳብ ቀርቧል፡፡
የመምህራን ማኅበር፣ የሠራተኛ ማኅበራት ኮንፌደሬሽን እና የአሠሪዎች ማኅበራት ኮንፌደሬሽን አመራሮች በረቂቅ አዋጁ ውይይት ላይ የተሳተፉ ሲሆን እንደ አገር መግባባት ላይ ሊደረስባቸው የሚገቡ ብዙ ጉዳዮች መኖራቸውን አንስተዋል፡፡
በመሆኑም የሚቋቋመው ኮሚሽን ተነጋግረን የምንግባባበትን መንገድ የሚፈጥር ሊሆን ይገባልም ማለታቸውን ከሥራ እና ክህሎት ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ አመላክቷል፡፡