የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ከሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ጋር የኦፕቲካል ፋይበር መስመር ኪራይ ሥምምነት ተፈራረመ

መጋቢት 2/2014 (ዋልታ) የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ከሳፋሪኮም-ኢትዮጵያ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ጋር የኦፕቲካል ፋይበር ኪራይ ሥምምነት ተፈራረመ፡፡

ሥምምነቱን የተፈራረሙት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈፃሚ አሸብር ባልቻ እና የሳፋሪኮም-ኢትዮጵያ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር  ዋና ሥራ አስፈፃሚ አንዋር ሶውሳ ናቸው፡፡

ሥምምነቱ በመጀመሪያ ምዕራፍ 4097 ኪ.ሜ፣ በሁለተኛው ምዕራፍ 2078 ኪ.ሜ እንዲሁም በሶስተኛው ምዕራፍ 2904 ኪ.ሜ የኦፕቲካል ፋይበር መስመር ኪራይን ያጠቃልላል ተብሏል፡፡

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈፃሚ አሸብር ባልቻ በፊርማ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ እንደተናገሩት ሥምምነቱ ሁለቱ ተቋማት በጋራ ተባብረው እንዲሰሩ መሠረት የሚጥል መሆኑን ገልጸው ተቋሙ ከኃይል ማመንጨት እና ማስተላለፍ ባሻገር የቴሌኮም ዘርፉን  ዲጂታል ለማድረግ በሚደረገው ጥረት ውስጥ የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ እንደሚገኝ አብራርተዋል፡፡

የሳፋሪኮም-ኢትዮጵያ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ዋና ሥራ አስፈፃሚ አንዋር ሶውሳ በበኩላቸው ኢትዮጵያ በቴሌኮም ዘርፍ እያሳየች ያለውን አዎንታዊ ዕድገት አድንቀው ሥምምነቱ ከተቋሙ ጋር ያለንን በጋራ የመሥራት ፍላጎት የሚያጠናክር ነው ብለዋል፡፡

ኩባንያቸው የዲጂታል ትራንስፎርሜሽኑን ለማሳካት በሚደረገው ርብርብ ውስጥ የበኩሉን አስተዋፅኦ ለመወጣት ዝግጁ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

ጥራትና ደረጃውን የጠበቀ የቴሌኮም አገልግሎት ለኅብረተሰቡ ለማቅረብም እየተሰራ መሆኑንም መግለፃቸውን ከኢትዮጵያ ኤሌክተሪክ ኃይል ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በመጀመሪያው ምዕራፍ የኦፕቲካል ፋይበር መስመር ኪራይ በዓመት እስከ 140 ሚሊዮን ብር ገቢ ያገኛል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል እስከ 15 ሺሕ ኪ.ሜ የሚሸፍን የኦፕቲከል ፋይበር መስመር ባለቤት ሲሆን ኢትዮ-ቴሌኮም 8745 ኪ.ሜ በኪራይ እንዲሁም ደግሞ ተቋሙ ለውስጥ የመረጃ ልውውጥ እየተጠቀሙበት ይገኛል፡፡