የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ለሚያስገነባው ባለ36 ወለል ህንጻ የመሰረት ድንጋይ ተቀመጠ

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት

ጥር 14/2014 (ዋልታ) የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ለሚያስገነባው ባለ36 ወለል ህንጻ የመሰረት ድንጋይ ተቀመጠ፡፡

ህንጻው በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የተደገፈና ተወዳዳሪ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል እንዲሁም ለከተማዋ ተደማሪ ውበት ነው ተብሏል።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሽፈራው ተሊላ እንደገለፁት ተቋሙ በየደረጃው እየተገለገለባቸው የሚገኙት ቢሮዎች ዋናው መስሪያ ቤትን ጨምሮ ለሰራተኞችና ደንበኞች ምቹ አይደሉም።

ቢሮዎቹም ኪራይ በመሆናቸው በተቋሙ ፋይናንስ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳደሩን ገልጸዋል፡፡

መሥሪያ ቤቱ በመጀመሪያው ዙር 19 ህንጻዎች፤ በ2ኛ ዙር 16 ህንጻዎችን ለመገንባት ቅድመ ዝግጅት ማድረጉን ዋና ሥራ አስፈጻሚው ጠቁመዋል፡፡

የዋናው መሥሪያ ቤት የመሰረት ድንጋይ በገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሽዴ የተቀመጠ ሲሆን ግንባታውም በ4 ዓመት ጊዜ ውስጥ ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

በመርሃ ግብሩ ላይ  የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሽዴ፣ የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስትር ሃብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር)፣ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ሥራ አመራር ቢርድ ሰብሳቢ ጌታሁን መኩሪያ (ዶ/ር)ን ጨምሮ ሌሎች የከፍተኛ የመንግስት ሥራ ኃላፊዎች፣ የተቋሙ ከፍተኛ አመራሮችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል፡፡

ግንባታዎቹ የሪጅን፣ የዲስትሪክትና አገልግሎት መስጫ ማዕከላት መሆናቸውም ተመላክቷል።

በአዲስ አበባ ፒያሳ የሚገኘው በተለምዶ ኤሌክትሪክ ህንጻ እየተባለ የሚጠራው የተቋሙ ዋና መስሪያ ቤት በ3 መቶ ሺሕ ብር የተገነባ፣ 156 ቢሮዎች ያሉት በ1946 ዓ.ም ተጀምሮ በ1948 የተጠናቀቀ የመጀመሪያው ባለ አሳንሰር ህንጻ እንደሆነም ይነገራል።

በተስፋዬ አባተ