የኢትዮጵያ እና ቻይና ግንኙነት በመርህ ላይ የተመሰረተና እኩልነትን መሰረት ያደረገ መሆኑን የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት ገለጹ

ግንቦት 9/2015 (ዋልታ) የኢትዮጵያ እና ቻይና ግንኙነት በመርህ ላይ የተመሰረተና እኩልነትን መሰረት ያደረገ መሆኑን የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አደም ፋራህ ገለጹ፡፡

የፓርቲው ምክትል ፕሬዝዳንት አደም ፋራህ በቻይና የናንዣ ግዛት የቻይና ኮሚኒስት ፓርቲ ኃላፊ በሆኑት ሊያንግ ሹን የተመራ የቻይና መንግስት ከፍተኛ የልኡካን ቡድንን በጽሕፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።

ዘመናትን በተሻገረው የኢትዮ ቻይና ወዳጅነት ሁለቱ ሀገራት በተለያዩ መስኮች በትብብር መስራታቸውን ያነሱት የፓርቲው ምክትል ፕሬዝዳንት ግንኙነቱ ወደተሻለ ደረጃ እንዲያድግ ብልፅግና ፓርቲ አተኩሮ እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ሁለቱ ሀገራት የፈጠሩት ግንኙነት ከውስጣዊ የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት የፀዳ፣ በመርህ ላይ የተመሰረተ እንዲሁም እኩልነትን መሰረት ያደረገ እንደሆነም ጠቅሰዋል።

አሁናዊ በሆነው የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ሁኔታ የቻይና የውጪ ቀጥታ ኢንቨስትመንት እየጨመረ መሆኑና ኢንቨስት የሚያደርጉ የቻይና ባለሀብቶች ቁጥራቸው እያደገ እንደሆነ ተናግረዋል።

በሁለቱ ሀገራት ጠንካራ ግንኙነት ምክንያትም ኢትዮጵያ ቤልት ኤንድ ሮድ ኢኒሼቲቭን በመሰሉ የቻይና መንግስት የልማት ፕሮግራሞች ተጠቃሚ መሆን እንደቻለችና ከ90 በመቶ በላይ የሚሆነው የኢትዮጵያ የገቢና ወጪ ንግድ የሚሳለጥበት የኢትዮ ጅቡቲ የባቡር መስመር የዚህ ትሩፋት ተጠቃሽ እንደሆነ ገልፀዋል።

ኢትዮጵያን በልማታዊ እንቅስቃሴዎች ከመደገፍ በላይ ብድሮችን በማራዘም እና የኢንቨስትመንት አማራጮችን በማስፋት ቻይና አጋርነቷን እያሳየች እንደሆነ ያነሱት የፓርቲው ምክትል ፕሬዝዳንት ይህንንም ብልፅግና ፓርቲ ልዩ ቦታ እንደሚሰጠው ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ከዚህ በፊት በቀኝ ግዛት ያልተገዛች እና ለመንግስታቱ ድርጅት ምስረታ ከፍተኛ አስተዋጽዖ እንደነበራት አውስተው ይህንንም በጎ ተፅእኖ በቀጣይ ለቻይና አፍሪካ ግንኙነት መዳበር እንደምትጠቀምበት አንስተዋል።

በቻይና የናንዣ ግዛት የቻይና ኮሚኒስት ፓርቲ ኃላፊ ሊያንግ ሹን በበኩላቸው ኢትዮጵያን በሁለንተናዊ መልኩ ለመደገፍ የቻይና መንግስት ቁርጠኛ መሆኑን ገልጸዋል።

የሲፒሲ እና የብልፅግና ፓርቲ ግንኙነት እንዲጠናከር፣ በመንግስታዊ ግንኙነቶችም ኢንቨስትመንቶች ፍሰታቸው እንዲያድግና የንግድ አማራጮች እንዲሰፉ በቀጣይ ሰፊ ስራዎች በቻይና መንግስት በኩል እንደሚሰሩ ቃል መግባታቸውን ከፓርቲው ጽሕፈት ቤት ያገኘነው መረጃ አመላክቷል።