የኢትዮጵያ ዋና ከተማ ሆና ያገለገለችው ባለብዙ ታሪክ ቀደምቷ ከተማ- ጎሬ

 

የኔ አገር

የኢትዮጵያ ዋና ከተማ ሆና ያገለገለችው ባለብዙ ታሪክ ቀደምቷ ከተማ- ጎሬ
በሠራዊት ሸሎ
ሚያዚያ 02/2015 (ዋልታ) የኔ አገር በይዘቷ ታሪክን ባህልን ኢሴቶችንና የቱሪስት መዳረሻ ቦታዎችን ታስተዋውቃለች፤ ታስቃኛለች፡፡በሣምንት አንዴ በሚታስቃኛቸው ይዘቷ ዛሬ ቀደምትና ብዙ ያልተነገራላትን ጎሬ ከተማን ይዛላችሁ ቀርባለች፡፡
ከቀደሙትና ታሪካዊ ከተሞች አንዷ ናት ይህች ባለ ብዙ የታሪክ ማህደሯ ጎሬ ከተማ።በአሁኑ ወቅት በኦሮሚያ ክልል በኢሉአባቦራ ዞን የአለ ወረዳ ዋና ከተማ ሲትሆን ከርዕሠ መድና አዲስ አበባ በ607 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ትገኛለች።
ዕድሜ ጠገቧና ጥንታዊቷ ይህች የጎሬ ከተማ የዘመናዊ ከተማ ቅርፅ እና አስተዳደር ይዛ የተመሰረተችው ከ1874 ዓ.ም ጀምሮ እንደነበር ይነገራል።
ከተማይቱ በዚያን በ19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የከተማ መሪ እቅድ እንደነበራትና በ1916 ዓመተ ምህረት የመሪ ዕቅድ እንደተዘጋጀላት መረጃዎች ያሳያሉ።የቀድሞ መንደሮቿና የገበያ ቦታዎች እንዲሁም በዚያ ወቅት የተሠሩ በየሰፈሩ የሚታዩ ጌጠኛ የድንጋይ ንጣፍ መንገዶች ዘመነኛና ከቀደምት ከተሞች አንዷ ስለመሆኗ ይናገራሉ።
በወቅቱ የኢሉባቦር ጠቅላይ ግዛት ሀገረ ገዢ የነበሩት ራስ ናደው አባ ወሎ ከተማዋን ለማዘመን ዓላማ ይዘው ጠጠርና ድንጋይ በማመላለስና ህብረተሰቡን በማስተባበር የከተማዋ ገጠኛ ድንጋይ ንጣፍ መንገዶች እንደተሰሩ ታሪክ ያስረዳል።
በወቅቱ መሠረታዊ አገልግሎት የሚሰጡና ወሣኝ የሆኑ የመሠረተ ልማት አውታሮች የተሟሉላት ከተማ እንደነበረችም ታሪክ ያወሳል።
በ1922 ዓመተ ምህረት የመብራት እንዲሁም በ1923 ዓመተ ምህረት የስልክ ተጠቃሚ የሆነችው ጎሬ ከ1929 ዓመተ ምህረት ጀምሮ የአይሮፕላን ማረፊያ የነበራትና እስከ 1992 ዓመተ ምህረት ድረስ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የአገር ውስጥ መዳረሻ ከተማ እንደነበረችም ይነገራል።
ከ1874 ዓመተ ምህረት ጀምሮ እስከ 1962 ዓ.ም ለ88 ዓመታት የቀድሞ ኢሉባቦር ጠቅላይ ግዛት ዋና ከተማ በመሆን አገልግላለች ቀደምቷ የጎሬ ከተማ፡፡
ይህች ቀደምትና የበርካታ ታሪክ ባለቤት የሆነችው ጎሬ ብዙ ያልተወራላት የምእራብ ኢትዮጵያ ፈርጥ በ1928 ዓ.ም በሁለተኛው የፋሺስት ጣልያን ወረራ ምክንያት የኢትዮጵያ ዋና ከተማ ሆና እንደተመረጠች ታሪክ ያስረዳል።
በወቅቱ በማይጨው የንጉሱ ጦር በመጠቃቱ እና የጠላት ጦር ወደ አዲስ አበባ ከተማ በመቃረቡ ምክንያት የኢትዮጵያ ዋና ከተማ ወደ ጎሬ እንዲዘዋወር ንጉሡ ሚያዝያ 5 ቀን1928 ዓ.ም ለፓርላማቸው አቅርበው ክርክር ከተደረገ በኋላ ለውሣኔ እንደተደረሰ መረጃዎች ያመለክታል።
በዕለቱ ለፖርላማ የቀረቡ የውሣኔ ሃሳቦች ሁለት እንደነበሩና እነዘህም የአገሪቱ ዋና ከተማ ከአዲስ አበባ ወደ ጎሬ የማዘዋወር እና የንጉሱ በአገር ውስጥ የመቆየት ጉዳይ እንደነበር ጣሪክ ያስረዳል።
የፓርላማ ውሣኔን ተከትሎ የጎሬ ከተማ ለተከታታይ 7 ወራት ከሚያዝያ 1928 ዓ.ም ጀምሮ እስከ ሕዳር 1929 ዓ.ም ድረስ የኢትዮጵያ ዋና ከተማ ሆና እንዳገለገለች መረጃዎች ይጠቁማሉ።
በከተማዋ ከእንግሊዞች አርመኖች፣ ግሪኮች፣ ሕንዶች እና አረቦች እንዲሁም ሌሎች የተለያዩ የውጭ አገር ዜጎች እንደነበሩ ይነገራል።
በወቅቱ በምዕራ ኢትዮጵያ ከሱዳን ጋር የነበረውን የንግድ እንቅስቃሴ ተከትሎ ልክ ድሬዳዋ የምሥራቋ በር እንደምትባል ሁሉ ጎሬ ደግሞ የምዕራቧ በር የተባለችበት ወቅት እንደነበር በከተማዋ የዕድሜ ባለፀጎች ይገለፃል።
ከ1906 ዓመተ ምህረት ጀምሮ እስከ1954 ዓመተ ምህረት ድረስ የእንግሊዝ ቆንፅላ ፅሕፈት ቤት ከአዲስ አበባ በተጨማሪ በጎሬ ከተማ እንደነበር ታሪክ ያስረዳል።
በአምስቱ የአርበኝነት ዓመታት ፋሽስት ኢጣሊያን ያርበደበደው የከተማዋና የአከባቢዋ አርበኞች ህያው ተጋድሎ ከተማይቱ የትግል ሜዳ እንደነበረችም ይነገራል።
ይህች ቀደምቷና ታሪካዊ ከተማ ብዙ ያለተነገረላቸው ጀብዶችና ለአገር ፍቅር ነፍሳቸውን እስከመስጠት ድረስ የተደረገ ጀግንነትን የፈጸሙ ባለታሪኮችን በጉያዋ ይዛዋለች፡፡
ጣልያን ከህዝቡ ተቀባይነትን ለማግኘት በማሰብ የሀይማኖት አባት የሆኑትን አቡነ ሚካኤልን ስለጣልያን መልካም ነገር ለምዕመናን እንዲያስተምሩ ነግሯቸው ኖሮ ጣልያን የሚባል መንግሥት በኢትዮጵያ የለም ጣልያን ወራሪ ነው እኛ የምናውቀው የኢትዮጵያን መንግስትን ነው በማለት ህዝቡ ጣልያንን እንዲያወግዘው በማስተማራቸውና በመገዘታቸው ወራሪው በመተሪየስ ገድሎአቸዋል ልክ እንደአቡነ ጰጥሮስ፡፡የኚህን ባለገድል አባት ታሪክ ጎሬን ሲጎበኙ ያገኙታል፡፡በጎሬ ከተማ የተሰራው የመታሰቢያ ሀውልታቸው ታሪካቸውን በጉልህ ያወራልና፡፡
ሌላው ደግሞ ዜጋው ለአገሩ ክብር ቋንቋ ባህልና እምነት ሳይገደበው ጣልያንን የተፈለመበትና ድል ያረገበት የሳንቤ ተራራ ነው፡፡በጎሬ ከተማ አጠገብ ሆኖ የጀግና አርበኞች ተጋድሎና ጀግኖች አርበኞች የተዋደቁለትን ህያው ታሪክ በጉልህ የሚናገረው ይህ ተራራ ብዙ ያልተነገረለት መሆኑም ይገለጻል፡፡ብቻ ጎሬ አገር ወዳድነትንና ጀግንነትን ፈቅርንና አብሮነትን አስተማሪ ታሪክ ያላት በመሆኗ ወደ ጎሬ ጎራ ያለው እዳች ጠቃሚ ነገር ይዞ ይመለሳል፡፡
የጎሬ ከተማን ቀደምትነት እና ታሪካዊነት የሚናገሩ መንደሮች እና የገበያ ስፍራዎች ሌላው አስተማሪና አስደማሚ ገጽታዋ ነው፡፡ሰማኒያና ከዚያ በላይ እድሜ ያስቆጠሩ ግን በአፈርና በድንጋይ ብቻ የተሠሩ ዕድመ ጠገብ ቤቶች ጥበብንና ለትውልድ አሳቢነትን መልዕክት ይለግሱናል፡፡እነዚያ በከተማይቱ የሚገኙ ዕድሜ ጠገብ ታሪካዊ ቤቶች በቅርስነነት መመዝገባቸውን መረጃዎች ይነግሩናል።
ዕድሜ ጠገቧና ጥንታዊቷ ይህች ከተማ ታሪኳ ጎልቶ እንዲወጣ ትውልዱ ታሪካዊ  ሃላፊነት አለው፡፡ጥንታዊነቷን የሚገልጹ ታሪካዊ መንደሮችና ቤቶች ይዘታቸውን ሳይለቁ ከተጠገኑና ለትውልድ ከቆዩ ታሪኳን ከማጉላት ባለፈ የቱርስት መዳረሻ እንዲትሆን ያደርጋታልና ሁሉም የድርሸውን ቢውጣ እንላለን፡፡