የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ለአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ አደረገ

ጥር 18/2014 (ዋልታ) የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በአሸባሪው የሕወሓት ወራሪ ጉዳት ለደረሰበት የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ድጋፍ አደረገ።

ድጋፉም ላፕቶፕ ኮምፒተሮች እንዲሁም ለአንድ ዓመት ነጻ የዜና አቅርቦት በድምሩ ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ አድርጓል።

በድጋፍ ርክክቡ ላይ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር)፣ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማዕከል አስተባባሪ ሚኒስትር ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር) እና የተቋማቱ የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

የመንግሥት የኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) አሚኮ ሕዝቡ አሸባሪውን የሕወሓት ወራሪ በተደራጀ መንገድ እንዲመክት ያደረገው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን አስታውሰው ተቋሙ በአሸባሪው ቡድን ከደረሰበት ዘረፋና ውድመት አገግሞ ወደ ሥራ ለመመለስ በሚያደርገው ጥረት የሚዲያ ተቋማት እያደረጉለት ያለው ድጋፍ የሚደነቅ መሆኑን ገልጸዋል።

በአገሪቷ በተፈጠሩ ትርክቶች ምክንያት የተፈጠሩ ልዩነቶች እንዲጠቡና የአገር ግንባታ ሂደቱ እንዲቃና የሚዲያ ተቋማት በጋራ መሥራት እንዳለባቸውም በማስገንዘብ ለግጭት ምክንያት የሆኑ ጉዳዮችን ለመፍታት አካታች አገራዊ ምክክር እንዲደረግ ሁኔታዎች እየተመቻቹ መሆኑንና የሚዲያ ተቋማትም ኅብረ ብሔራዊ አንድነት ለመፍጠር በጋራ ሊሰሩ እንደሚገባ ተናግረዋል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማዕከል አስተባባሪ ሚኒስትር ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር) አሚኮ ኢትዮጵያዊነት እንዲጎለብትና በዜጎች መካከል መቀራረብ እንዲፈጠር ሲሰራ መቆየቱን አንስተዋል።

80ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን የሚያከብረው የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ካለው ላይ ቀንሶ ለአሚኮ ያደረገው ድጋፍ ወንድማማችነትን የሚያጠናክር መሆኑን ገልጸው ድጋፉ ተቋማቱ ለጋራ ዓላማ የሚሰሩ በመሆናቸው የራስን ሚዲያ እንደማጠናከር ነው በሚል የተደረገ በመሆኑ ኢዜአ ሊመሰገን ይገባል ብለዋል። ይህ መደጋገፍ ለሌሎች ተቋማትም ዓርአያ ይሆናል ብለዋል።

የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሙሉቀን ሰጥዬ በበኩላቸው አሸባሪው ሕወሓት በምስራቅ አማራ የሚገኙ የተቋሙን ከስድስት በላይ የሬዴዮ ማሰራጫና አገልግሎት መስጫዎች ማውደሙን ገልጸዋል።

ይሁንና ሚዲያውን መልሶ ወደ ሥራ ለማስገባት በተከናወኑ ተግባራት አብዛኞቹ ማሰራጫዎች ወደ ሥራ መመለስ መቻላቸውን ተናግረው ተቋሙን ወደ ሥራ ለመመለስ ድጋፍ በማድረግ አጋርነታቸውን ካሳዩ የመገናኛ ብዙኃን ተቋማት መካከል ኢዜአ አንዱ መሆኑን በመጥቀስ መስጋና አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሰይፈ ደርቤም ተቋሙ ያደረገው ድጋፍ የሁለቱን ተቋማት ግንኙነት የሚያጠናክር መሆኑን ገልጸው ኢዜአ ባለፉት 80 ዓመታት በሚሰጣቸው አገልግሎቶች ከተለያዩ የሚዲያ ተቋማት ጋር በርካታ ውጣ ውረዶችን በጋራ ያለፈ መሆኑን ማንሳታቸውን ከተቋሙ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።