የኢትዮጵያ የሐይማኖት ተቋማት ጉባኤ ከአገር ውጪ የመጀመሪያውን የመመስረቻ ጉባኤ አካሄደ

ግንቦት 14/2013 (ዋልታ) – የኢትዮጵያ የሐይማኖት ተቋማት ጉባኤ የሠላም ግንባታ ፣የአብሮነትና የመከባበር የጋራ ዕሴቶችን አጠናክሮ ለመስራት የሚያስችለውን የመመስረቻ ጉባኤ ከአገር ውጪ ለመጀመሪያ ጊዜ በአሜሪካን አካሄደ።
አሜሪካን ዋሽንግተን በሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ የኢትዮጵያ የሐይማኖት ተቋማት ጉባኤ ዋና ጸሐፊ ሊቀ ትጉኃን ቀሲስ ታጋይ ታደለ የሐይማኖት ተቋማት ተወካዮችና በአሜሪካ የኢትዮጵያ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ፍጹም አረጋ በተገኙበት የሀይማኖት ተቋማት ጉባዔ ተካሂዷል።
እንደ ኢዜአ ዘገባ በዚህ ወቅት የሐይማኖት ተቋማት ጉባኤ ዋና ጸሐፊ ሊቀ ትጉኃን ታጋይ እንዳሉት “ከሁሉም ቤተ እምነት ከተወከሉ የሃይማኖት አባቶች ጋር በጉዳዩ ሰፊ ውይይት ከተደረገ በኋላ ከአገር ውጪ የመጀመሪያውን የመመስረቻ ጉባኤ ተካሂዷል”።
በዚህም የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ የጋራ ዕሴት የሆነውን የሠላም ግንባታ ፣የአብሮነትና የመከባበር ተግባራትን አጠናክሮ ለመስራት ሀገራዊና ተቋማዊ ጥንካሬ እንዲፈጠር የጉባኤው መመስረት ጉልህ ሚና እንዲኖረው ያስችላል ብለዋል።