የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ለችግር ለተጋለጡ ዜጎች ከ430 ሚሊየን ብር በላይ ድጋፍ አደረገ

ሚያዝያ 28/2013(ዋልታ) – የኢትዮጵያ ዳያስፖራ የተለያዩ አካባቢዎች በተፈጠሩ የጸጥታ ችግሮች ምክንያት ለጉዳት ለተጋለጡ ዜጎች ከ430 ሚሊዮን ብር በላይ የገንዘብና የአይነት ድጋፍ ማድረጉ ተገለፀ፡፡
በበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት ከዳያስፖራ ከ236 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጣ ሀብት የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ለመከላከል ለሚከናወኑ ስራዎች መሰብሰቡንም ገልጿል።
መንግስት በጥቅምት ወር “የሕወሓት ቡድን” በሰሜን ዕዝ የመከላከያ ሰራዊት ላይ የፈጸመውን ጥቃት ተከትሎ በትግራይ ክልል የሕግ ማስከበር እርምጃ መውሰዱ ይታወቃል።
በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች በተከሰቱ የጸጥታ ችግሮችና በንጹሃን ዜጎች ላይ በሚደርሱ ጥቃቶች ዜጎች ለችግር እየተጋለጡም መሆኑ ይታወቃል።
የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሰላማዊት ዳዊት ዳያስፖራው ለተቸገሩ ወገኖችና ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ተቋማት ድጋፍ ማሰባሰብ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ሀሳብ ማቅረቡን ገልጸዋል።
ኤጀንሲው የቀረበውን ሀሳብ ተከትሎ ፕሮጀክት በመቅረጽ ወደ ድጋፍ ማሰባሰብ ስራ መግባቱንና እስካሁን ዳያስፖራ በገንዘብና በአይነት ከ431 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ማድረጉን የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲን ጠቅሶ ኢዜአ ዘግቧል።