የኢትዮ-ሱዳን የወዳጅነት ባህል ምሽት ተካሄደ

የካቲት 2/2014 (ዋልታ) የኢትዮ-ሱዳን ወዳጅነት ማኅበር በሱዳን ከኢ.ፌ.ዲ.ሪ ኤምባሲ ጋር በመተባበር የባህል ምሽት በካርቱም አካሂዷል፡፡

በመርሃግሩ በሱዳን የኢትዮጵያ አምባሳደር ይበልጣል አዕምሮ የሁለቱ አገራት ሕዝቦች ትስስር ዘርፈ ብዙና ታሪካዊ፣ የወደፊት እጣፋንታቸውም የተሳሰረ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የሱዳን እና የኢትዮጵያ ሕዝቦች ተመሳሳይ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና የፖለቲካ ችግሮች ያሉባቸው ሕዝቦች በመሆናቸው በመካከላቸው ያለውን መደጋገፍ በማጠናከር የጋራ ችግሮችን ለመቅረፍ በጋራ ሊሰሩ ይገባል ያሉት አምባሳደሩ የሁለቱን ሕዝቦች ሁለንተናዊ ትስስር ለማጎልበት የኢትዮጵያ በኩል ያለውን ዝግጁነት አረጋግጠዋል፡፡

የሱዳን ዓለም ዐቀፍ ሕዝቦች የወዳጅነት ምክር ቤት ዋና ፀሐፊ ሳልዋ መሃመድ በበኩላቸው የሁለቱ አገሮች ሕዝቦች ተመሳሳይ የቆዳ ቀለም፣ የጋራ ባህል እና የጋራ ታሪክ ያላቸው ሕዝቦች መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

የአንዱ አገር ዜጋ በሌላው በነፃነት የሚኖር እንዲሁም በሰው ሠራሽ ድንበር የተለየ በሁለት አገር የሚኖር አንድ ሕዝብ መሆኑን አንስተው ይህን የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ለማጠናከር በጋራ ለመሥራት ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል፡፡

በመርሃግብሩ ላይ የተለያዩ አገራት አምባሳደሮች መታደማቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽሕፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡