የኢትዮ-ሳዑዲ ንግድና ኢንቨስትመንት ፎረም መካሄድ ጀመረ

ግንቦት 28/2016 (አዲስ ዋልታ) የኢትዮ-ሳዑዲ ንግድና ኢንቨስትመንት ፎረም በአዲስ አበባ መካሄድ ጀመረ።

በሳዑዲ አረቢያ የንግድ ምክር ቤት ፌዴሬሽን የተመራ 79 አባላትን የያዘ ከፍተኛ የኢንቨስትመንት እና የንግድ የልዑካን ቡድን ኢትዮጵያን ለመጎብኘት ትላንት ማምሻውን አዲስ አበባ መግባቱ ይታወቃል።

ይህንን ተከትሎም የሁለቱ ሀገራት የቢዝነስ ፎረም ዛሬ በአዲስ አበባ መካሄድ ጀምሯል።

የሳዑዲ ልዑካን ቡድን ከፎረሙ አስቀድሞ የኢትዮጵያን የቆዳ፣ ጨርቃጨርቅ፣ ማዕድንና ሌሎች ምርቶችን እንዲሁም የቱሪዝም መዳረሻዎችን የሚያሳይ አውደ-ርዕይን ጎብኝተዋል።

በፎረሙ ላይ የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር)፣ የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር)፣ የቱሪዝም ሚኒስትር አምባሳደር ናሲሴ ጫሊ፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።

የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር) በዚህ ወቅት በኢትዮጵያና ሳዑዲ አረቢያ መካከል ታሪካዊ የንግድና ኢንቨስትመንት ግንኙነት መኖሩን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ኢንቨስትመንትን የሚያበረታታ ሁለተኛውን ምዕራፍ የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ መተግበር መጀመሯንም ጠቅሰዋል።

መንግስት የንግድ ዘርፉን ለውጭ ባለሀብቶች ክፍት ማድረጉን ጠቅሰው ከህግ፣ ከአሰራርና ከመሰረተ ልማት አኳያም የውጭ ኢንቨስተሮችን የሚያበረታታ ምቹ ምህዳር መኖሩን አንስተዋል።

በመሆኑም የሳዑዲ ባለሀብቶች በማምረቻ፣ በቱሪዝም፣ በማዕድን፣ በታዳሽ ኃይልና ሌሎች የኢንቨስትመንት መስኮች እንዲሰማሩ ጥሪ ማቅረባቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

የሳዑዲ አረቢያ የንግድና ኢንቨስትመንት ልዑካን ቡድን በኢትዮጵያ እያደረገ ያለው ጉብኝት የሁለቱን ሀገራት ኢኮኖሚያዊ ትስስር ለማጠናከር ያለመ ነው ተብሏል።

ልዑኩ በአዲስ አበባ በሚኖረው የሶስት ቀናት ቆይታ ስትራቴጂያዊ ጠቀሜታ ያላቸውን የማምረቻ ቦታዎችን እንደሚጎበኝ እንዲሁም የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤትና የሳዑዲ አረቢያ አቻው የመግባቢያ ስምምነት እንደሚፈራረሙ ይጠበቃል።