ግንቦት 18/2013 (ዋልታ) – በኢትዮጵያ እና ኦማን መካከል የንግድ እና ኢንቨስትመንት ግንኙነትን ማሳደግ ላይ ያተኮረ የበይነ መረብ ፎረም ተካሄደ፡፡
በፎረሙ ላይ በግብርና፣ ኢነርጂ እና ማዕድን ዘርፍ የተሰማሩ ከ70 በላይ ተሳታፊዎች መገኘታቸው ተገልጿል።
በኦማን የኢፌዴሪ አምባሳደር ዶ/ር አይሮሪት መሐመድ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር ፎረሙ በሁለቱ ሀገራት መካከል በንግድ፣ ኢንቨስትመንት፣ ቱሪዝም እና ቴክኖሎጂ ሽግግር ዙሪያ ትብብርን ለማሳደግ አመቺ ሁኔታ ይፈጥራል ብለዋል።
የንግድ እና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አረጋ በበኩላቸው፣ ፎረሙ የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት እንደሚያጠናክር ጠቅሰዋል።
የኦማን የንግድ፣ ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ሚኒስቴር ቋሚ ተጠሪ የሆኑት አሰላ ሳልም ደግሞ ኢትዮጵያን ጨምሮ የአፍሪካ ሀገራት የገበያ ዕድሎችን ለመጠቀም ሀገራቸው በትኩረት እየሠራች መሆኑን አስረድተዋል።
በኢትዮጵያ ሰፊ የገበያ ዕድል እንዳለ የጠቀሱት ቋሚ ተጠሪዋ፣ በሁለቱ ሀገሮች የቢዝነስ ሰዎች በመቀራረብ በጋራ መሥራት አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል።
የኦማን የንግድ እና ኢንዱስትሪ ዘርፍ ማኅበራት ሊቀ-መንበር ሁለቱ ሀገሮች በኢኮኖሚ ጉዳዮች ስምምነት እንዲፈራረሙ በተለይም ኢንቨስትመንትን ማስተዋወቅ እና የኢንቨስትመንት ጥበቃ እና ተደጋጋሚ ቀረጥ ማስቀረት ስምምነት ዙሪያ መሠራት እንዳለበት አስተያየት መስጠታቸውን ከሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ ጽ/ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።