የኢትዮ-ጂቡቲ የከባድ መኪና አሽከርካሪዎች የሚገጥማቸውን ችግር ለመፍታት እየተሠራ ነው

ግንቦት 21/2014 (ዋልታ) የኢትዮ-ጂቡቲ ከባድ መኪና አሽከርካሪዎች በአፋር ክልል የሚገጥማቸውን ችግር ለመፍታት ክልሉ ከፌዴራል መንግሥት ጋር በመተባበር እየሠራ መሆኑን ገለጸ።
የክልሉ የመንገድ ልማትና ትራንስፖርት ቢሮ የኢትዮ-ጂቡቲ ከባድ መኪና አሽከርካሪዎች በክልሉ የጸጥታና የመልካም አስተዳደር ችግሮች እያጋጠሟቸው እንደሆነ ማረጋገጡን ገልጿል።
ችግሩን ለመፍታት በየደረጃው ከሚመለከታቸው የክልልና የፌዴራል አካላት ጋር በትኩረት እየሠራ መሆኑን ገልጿል።
የኢትዮ-ጂቡቲ ከባድ መኪና አሽከርካሪዎች ከክልሉ የመንገድ ልማትና ትራንስፖርት ቢሮ ጋር በሰመራ-ሎጊያ ባደረጉት ውይይት በክልሉ ችግር እየገጠማቸው መሆኑን ገልጸዋል።
የከባድ መኪና አሽከርካሪዎቹ በተለይም ከእንድፎ እስከ ሚሌ ድረስ ባለው መስመር መሳሪያ የታጠቁ ሰዎች መንገድ በመዝጋት ዝርፊያና ተያያዥ ወንጀሎች እንደሚፈጽምባቸው ተናግረዋል።
ጓደኞቻቸውን በአካባቢው ታጣቂዎች በሚተኮስ ጥይት እንዳጡ ጠቅሰው በመሆኑም የሚመለከተው አካል በሥርዓት አልበኞች የሚፈጸመውን የደኅንነት ሥጋት እንዲያስቆምላቸው ጠይቀዋል፡፡
ሕጋዊነታቸውን የሚገልጽ ምንም አይነት መለያ ያላደረጉ የመንገድ ትራንስፖርት ተቆጣጣሪዎች ነን የሚሉ ሰዎች እንደሚያጉላሏቸው፣ ገንዘብ እንደሚጠይቋቸው እና አካላዊ ጥቃት እንደሚያደርሱባቸውም አሽከርካሪዎቹ አስረድተዋል።
ከአዋሽ እስከ ጋላፊ ድረስ ባለው መንገድም የመንገድ ትራንስፖርት ተቆጣጣሪዎች እና ትራፊክ ፖሊሶች “እጅ መንሻ” ገንዘብ በግልጽ እንደሚጠይቋቸውም ነው የገለጹት።
የክልሉ የመንገድ ልማትና ትራንስፖርት ቢሮ የአሽከካሪና ተሽከርካሪ ሥምሪት ዳይሬክተር ሁሴን ቦሎኮ የአሽከርካሪዎቹ ደኅንነትና ሠላም መረጋገጥ ከሀገር ሠላምና ደኅንነት ጋር በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የተቆራኘ በመሆኑ የክልሉ መንግስት ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ኃላፊነቱን በብቃት እንደሚወጣ አረጋግጠዋል።
ከአሽከርካሪዎቹ የተነሱት ችግሮች መኖራቸውን ጠቅሰው ችግሮቹን ለመፍታት በትኩረት እየተሰራ መሆኑን አመላክተዋል።
በተለይም የመንገድ ተቆጣጣሪዎች በከባድ መኪና አሽከርካሪዎች ላይ የሚፈጥሩት መጉላላትና እንግልት ለማስቀረት ተቆጣጣሪዎቹ ከባድ መኪና እንዳያስቆሙ ትዕዛዝ መተላለፉንም የኢዜአ ዘገባ አመላክቷል፡፡