የኢንዱስትሪ ፓርክ ሰራተኞች ለሚያነሱት ተገቢ የደሞዝ ጥያቄ ባለድርሻ አካላት በቅንጅት ሊሰሩ እንደሚገባ ተገለጸ

መጋቢት 07/2013 (ዋልታ) – በኢንዱስትሪ ፓርኮች በሚሰሩ ሰራተኞች ለሚነሱ ተገቢ የደሞዝ ጥያቄዎች መልስ ለመስጠት የሚመለከታቸው አካላት በቅንጅት ሊሰሩ እንደሚገባ የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ገለፀ፡፡

የሰራተኛ እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር በበኩሉ ለደሞዝ ጥያቄው ዘላቂ ምላሽ ሊሆን የሚችለው ዝቅተኛ የደሞዝ መነሻ እንደ ሀገር ሲቀመጥ መፍትሔዎች ይመጣሉ ብሏል፡፡

ፓርኮቹ ስራ አጥነትን በመቀነስ ረገድ እየተወጡት ያለው ሚና ከፍተኛ ቢሆንም ለሰራተኞቹ ምቹ የስራ አከባቢን መፍጠር ካልቻሉ ምርታማነት ላይ አሉታዊ ተፅእኖን ያሳድራሉም ብለዋል ዋልታ ያናገራቸው የምጣኔ ሀብት ባለሙያ፡፡

ይሁንና የሚፈጠረው የስራ እድል ከቁጥር ባለፈ የሰራተኞቹን ህይወት በሚቀይር ደረጃ ውጤታማ የመሆን ጉዳይ ላይ ግን ጥያቄዎች ይነሳሉ ፡፡ በተለይም የሚከፈላቸው ደሞዝ ጋር በተያያዘ ቅሬታዎች ያሰማሉ፡፡

ጥያቄው የሰራተኞቹ ብቻ ሳይሆን የእኛም ነው ሲሉ የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ኮርፖሬሽን ስራ አስፈፃሚ ገልጸዋል፡፡

የኢንዱስትሪ ፓርኮች ኮርፖሬሽን ኢንዱስትሪዎች ለሰራተኞች የደሞዝ ማሻሻያ የማድረግ ፍላጎት ሳይኖራቸው ቀርቶ ሳይሆን እንደ ሀገር የዝቅተኛ ደሞዝ ወለል ባለመቀመጡ ነውም ብለዋል፡፡

ዋልታ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው የመንግስት መስሪያ ቤቶች ፊት ተጠቃሽ የሆነው የሰራተኛ እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ዝቅተኛ የደሞዝ መነሻን የማስቀመጥ ሀገራዊ እቅዱ ትግበራ ከወዴት አለ ሲል ጠይቋል፡፡

(በድልአብ ለማ)